የሌማት ትሩፋት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚሆን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

532
እንጅባራ: ሕዳር 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የሌማት ትሩፋት የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በቻግኒ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ፀጋ ቢኖራትም እስካሁን በምግብ እራስን አለመቻል ያስቆጫል ብለዋል። ችግሩን ለመቅረፍ አዲስ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት የጠቆሙት ርእሰ መሥተዳደሩ ከእነዚህ አሠራሮች ውስጥ አንዱ የሌማት ትሩፋት ትግበራ መኾኑን ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋትን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትና ትግል እንደሚጠይቅም ነው ርእሰ መሥተዳደሩ ያስገነዘቡት። የሌማት ትሩፋትን ለመተግበር የአማራ ክልል የተሟላ ፀጋ እንዳለውም አንስተዋል። ርእሰ መሥተዳደሩ እንዳሉት የሌማት ትሩፋትን ለማሳካት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የአሠራርና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ተገቢ ነው። ርእሰ መሥተዳደሩ እንደተናገሩት የሌማት ትሩፋትን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ይገባል።
በክልሉ የሌማት ትሩፋት ስኬታማ እንዲኾን በተለይ አመራሩና ባለሙያው በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። ርእሰ መሥተዳደሩ እንዳሉት አርሶአደሮች የእንስሳት አረባብ ዘዴን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።
ርእሰ መሥተዳደር ዶክተር ይልቃል ለሌማት ትሩፋት ውጤታማነትና ትግበራ መላው የክልሉ ሕዝብ ተባባሪ ሊኾን እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleʺየንጉሥ ሚካኤል አሻራ፣ የረቀቀው ሙሽራ”
Next articleʺቢያወጣልኝ ብሎ የፍቅሩን ትኩሳት፣ የጋፋትን አፈር አቀለጠው በእሳት”