ʺየንጉሥ ሚካኤል አሻራ፣ የረቀቀው ሙሽራ”

203
ባሕር ዳር: ሕዳር 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብልሆች በብልሃት ይኖራሉ፣ ጠቢባን በጥበብ ይሠራሉ፣ ለጥበብ ይኖራሉ፣ ጀግኖች በጀግንነት ይከበራሉ፣ በጀግንነት ያስከብራሉ፣ ሩቅ አሳቢዎች ዛሬ ላይ ኾነው ነገን ያበጃሉ፣ ትውልድን ያስባሉ፣ መልካም ለመልካም ሥራ ይታትራሉ፡፡ በምድር የረቀቀውን፣ አጀብ የሚያሰኘውን፣ ታሪክ ጎላ አድርጎ የሚጽፈውን፣ ትውልድ ሁሉ ሲያመሰግነው የሚኖረውን ይሠራሉ፡፡
መልካም ሠርተው ያለፉት ነብሳቸውን ይማረው፣ ዘራቸውን ይባርከው፣ ትውልዳቸውን ክፉ አይንካው ሲባሉ ይኖራሉ፣ አልፈው እንኳን እንዳሉ ኾነው ይከበራሉ፣ ዘመን አልፎ ዘመን በመጣ ቁጥር ይዘከራሉ፣ ከከፍታው ላይ በክብር እንደተቀመጡ ዘመናትን ይሻገራሉ፡፡ ሞቶ የማይቀበር፣ ወድቆ የማይሰበር፣ ትውልድ ሲያነሳው፣ ታሪክ ሲያሞግሰው፣ ወገን ሲኮራበት፣ ሲከበርበት፣ ትናንትን ሲያሳይበት፣ ዛሬን ሲደምቅበት፣ ነገን ሲያሳምርበት የሚኖር ስምና ታሪክ ትተው የሚያልፉት እንዴት የታደሉ ናቸው?
ገጣሚያን ይገጥሙላቸዋል፣ ዓለም አጫዋቾች ይቀኙላቸዋል፣ ታሪክ አዋቂዎች ስማቸውን እየደጋገሙ ያነሷቸዋል፣ የጦር አበጋዞች ዝናቸውን እያነሱ ይፎክሩባቸዋል፣ ይመኩባቸዋል፣ ጋሻና ከለላ፣ ጥላና መከታ ያደርጓቸዋል፡፡ ታላቅ ግርማ ያላቸው፣ ማስታዋል የተቸራቸው፣ ጀግንነት የበዛላቸው፣ ለቃላቸው የሚኖሩ፣ ላመኑበት የሚሠሩ ኃያል ናቸው ይሏቸዋል፡፡
በሚወዷት ሀገራቸው ላይ ጠላት በተነሳ ቁጥር ዘራፍ ብለው ተነስተዋል፣ ጦር አስከትለው ዘምተዋል፣ ተዋግተው ድል አድርገዋል፣ አዋግተው ሀገር አስከብረዋል፡፡ አባ ሻንቆ እየተባሉ ተፎክሮላቸዋል፣ አባ ሻንቆ እየተባሉ በስማቸው ተምሎላቸዋል፡፡ የሰዓቲው ዘማች፣ የመተማው አርበኛ፣ የዓድዋው ጀግና፣ የወሎው ባላባት፣ የተንታው ልዑል፣ የአይጠየፉ ጌታ ንጉሥ ሚካኤል፡፡
ዶክተር ምስጋናው ታደሰ ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ በሚለው መጽሐፋቸው ንጉሥ ሚካኤል በሰዓቲ፣ በመተማ እና በዓድዋ በተካሄዱ ዘመቻዎች በርካታ ሠራዊት ይዘው የዘመቱ፣ የተዋጉና ሀገርን ያስከበሩ ጀግና መኾናቸውን ጽፈዋል፡፡ ሚካኤል በርካታ የጦር ሠራዊት ይዘው እየዘመቱ የጠላትን አንገት የሚያስደፉ ጀግና የጦር መሪ፣ የጠላትን ቅስምና አንገት ሰባሪ፣ ወገንን አኩሪ መኾናቸው ይነገራል፡፡
የምኒልክ አማች፣ የሸዋረጋ ባለቤት፣ የልጅ ኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል በዘመናቸው አያሌ ታሪኮችን ሰርተዋል፡፡ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳባቸው፣ ክብራቸው የሚገለጥባቸው፣ ታላቅነታቸው የሚመሰከርባቸው የረቀቁ የታሪክ አሻራዎችን አስቀምጠዋል፡፡
ʺማን በነገረው ለጣልያን ደርሶ
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ” የተባለላቸው ሚካኤል ኢትዮጵያውያንን ባኮራው፣ ጣሊያንን ባሳፈረው፣ ነጭን ባስደነገጠው፣ ጥቁርን ከፍ ከፍ ባደረገው የዓድዋ ጦርነት ከነበሩ የጦር አበጋዞች አንደኛው ናቸው፡፡ የበዛ ፈረሰኛና እግረኛ ሠራዊት አስከትለው ዘምተው ኢጣሊያን ድል አድርገው በኩራት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተመልሰዋል፡፡
ሚካኤል እትብታቸው በተቀበረበት፣ ዙፋናቸውን ባሳረፉበት፣በፍቅርና በክብር በገዙበት በወሎ የከበሩ አሻራዎች አሏቸው፡፡ ንጉሡ በወሎ ካሳረፏቸው አሻራዎች፣ እሳቸውም ከስጋ ድካም ያረፉበት አንደኛው የተንታ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ተንታ ንጉሥ ሚካኤል ማዕከላቸውን አድርገው ወሎን ያስተዳደሩባት፣ ከእርሳቸው አስቀድመው የነበሩ ገዢዎችም መናገሻቸው ያደረጓት፣ መኳንንትና መሳፍንንት የኖሩባት ታሪካዊት ሥፍራ ናት፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ሃይማኖታቸውን አክባሪ፣ ደብር ደባሪ፣ መልካም ሥራ ሠሪ፣ አዛኝና ሩህሩህ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ዶክተር ምስጋናው ታደሰ ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ በሚለው መጽሐፋቸው በተንታ ሚካኤል ከሚገኝ መጽሐፍ ዋቢ አድርገው ሲገልጹ ʺ ሚካኤል ለችግረኞች ምጽዋትን ይሰጥ፣ የተራቆቱትንም ያለብስ ነበር፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ከድሆች ጋር አብረው የሚበሉ፣ ምጽዋት መስጠትን የሚያዘውትሩ ደገኛ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው ሚካኤል ኾይ እንደ አንተ ያለ ለጋስ የለም የሚባልላቸው ለጋስም ነበሩ፡፡ የንጉሥ ሚካኤል አሻራ፣ የረቀቀው ሙሽራ የተንታ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን በመምህር አካለ ወልድ ሃሳብ ሰጪነት፣ በሚካኤል አባት መቃብር ላይ የተሠራ መኾኑን ዶክተር ምስጋናው ጽፈዋል፡፡
ንጉሡ በተንታ የሚካኤል ደብርን አሳምረው ደበሩ፡፡ አስውበው አከበሩ፡፡ ይህ ቤተክርስትያን ንጉሡ ካሳነጿቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል እጅግ የተዋበውና ያማረው እንደኾነ ይነገራል፡፡ ይህን ቤተክርስትያን በረቀቀ ጥበብ ሊያሠሩ ከውጭ ሀገር ባለሙያዎችንም አስመጥተዋል፡፡
ሥራውን የሚሠሩ ባለሙያዎች ብቻ ሳይኾኑ መሥሪያዎችም ከውጭ ሀገር የመጡለት፣ ሚካኤል እየተከታተሉ ያሠሩት፣ ድንቅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ያረፈበት ቤተክርስትያን ነው ተንታ ሚካኤል፡፡ ተንታ ሚካኤል ያጌጡ ድንጋዮች፣ የተመረጡ እንጨቶች የገቡበት፣ አናጢዎች በከፍተኛ ጥበብ የሠሩት ነው፡፡ እንጨቱ ሳልመኔ ከተባለች ሥፍራ እየተጓዘ እንደመጣም ዶክተር ምስጋናው ጽፈዋል፡፡
ንጉሥ ሚካኤል የተንታ ሚካኤልን ፍጻሜ ለማየት ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ መሐንዲሱን ሚካኤል ሚኮቪችን ʺ ሳልሞት ይህ ቤተክርስትያን ተጠናቆ አየው ይሆንን?” ብለው ጠየቁት፡፡ መሐንዲሱም ʺ እኔ ሚካኤል፣ አንተ ሚካኤል የሚሠራው ሚካኤል እንዴት ፍጻሜውን ሳታይ ትሞታለህ?” አላቸው ይላሉ፡፡
የተንታ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን አስተዳደሪ መላከ ብርሃን ተመስገን ተገኘ የተንታ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰባት ዓመታት ከሰባት ቀናት የግንባታ ጊዜ እንደ ወሰደበት አባቶቻችን ነግረውናል ብለውኛል፡፡ ሕንጻ ቤተክርስትያኑ ተጠናቅቆ ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ጳጳሱ፣ ቀሳውስቱ፣ ዲያቆናቱ፣ መዘምራኑ እና አንባቢያኑ፣መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ የጦር አበጋዞች ተገኝተው እንደነበር ይነገራል፡፡ በስስት እያዩት ኖረው የተመረቀ ቤተክርስትያን ነውና በታላቅ ደስታ ተመረቀ ይላሉ፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት ጋር አዋደው የያዙ፣ የረቀቀ ቤተ መቅደስ ያሳነፁ ብልሕ ንጉሥ ናቸው ይሏቸዋል መላክ ብርሃን ተመስገን፡፡ ተንታ ሚካኤል እጅግ የረቀቀ ቤተ መቅደስ፣ ታይቶ የማይጠገብ ደብር ነው፡፡ አበው የሚኖሩበት፣ ሊቃውንት የሚፈልቁበት፣ ዲያቆናት የሚገኙበት፣ የታሪክ አሻራና ጥበብ የበዛበት ታላቅ ነው፡፡ ያን የመሰለ ደብር አይቶ የማይደነቅ፣ ያን የመሰለ ቤተ መቅደስ ተመልክቶ እፁብ የማይል የት ይገኛል፡፡
በዚሕ ታላቅ ቤተክርስትያን የንጉሡ የራስ ዘውዳቸው፣ የአንገት መስቀላቸው፣ ከስጋ ድካም ሲያርፉ ያረፉበት መቃብራቸው፣ የንጉሡ አልባሳት፣ ጋሻና ጦራቸው፣ ለቤተ ክርስትያኑ ያበረከቷቸው ንዋየ ቅድሳት፣ በብርና በወርቅ የተሠሩ መስቀሎች፣ ያማሩ ምንጣፎች፣ መጻሕፍትና ሌሎች ታሪካዊ መንፈሳዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ለሚወዱት ደብር ታላላቅ ስጦታዎችን ሰጥተው ማለፋቸውንም ነግረውኛል፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ልጆቼ ኾይ አደራ፣ ታሪክን ጠብቁ፣ የሰው ልጅ ይሞታል፣ ታሪክ ግን አይሞትም፣ በምድር የሰጠኋችሁን በሰማይ እቀበላችኋለሁ አደራ ብለዋል፣ የእሳቸውን ቃል የተቀበሉ ልጆችና የልጅ ልጆችም ቃላቸውን እየጠበቁ ታሪካቸውን እያስከበሩ ነው ብለውኛል፡፡ ለቅርሶቹ መቀመጫ ይኾን ዘንድ ቤተ መዝክርም ተሠርቶለታል፡፡ የሀገር ኩራትና ሃብት የኾነው ታላቁን ቤተክርስትያን ሕዝብ ሁሉ እየመጣ እንዲያዬውም መላከ ብርሃን ተመስገን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የንጉሡ ታላቅ አሻራ ያለበት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃብት መኾኑንም ነግረውኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን እያወቁ እንዲጠብቁም አደራ ብለዋል፡፡
ወደ ተንታ ገስግሱ ንጉሥ ሚካኤል ታላቅ ነገር ወደ አደረጉበት፣ ስማቸውን ከመቃብር በላይ አስቀምጠው ወደ አረፉበት፣ የረቀቀ ቤተክርስቲያን ወደ አሠሩበት፣ አባ ሻንቆ በፈረሳቸው ላይ ተቀምጠው ወደ ሚታዩበት፡፡ ኢትዮጵያን ይወቋት፣ አውቀውም ያድንቋት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የአማራ ክልል በሚገባው ልክ እንዳያድግ ያደረገው በኃይል አቅርቦት ላይ የተሠራው መዋቅራዊ ሥራ ነው” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
Next articleየሌማት ትሩፋት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚሆን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።