አዴፓ ከውህደቱ ቀድሞ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ምሁራን ተናገሩ፡፡

232

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢህአዴግን ውህደት በተመለከተ በውይይት ሕዝበን ሊጠቅም ወደሚችል መንገድ መግባት እንደሚገባ ምሁራን መክረዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ደሞዝ ካሴ እና የፖለቲካ ፍልስፍና መምህር አቶ ሰለሞን አምባው በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከአብመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢህአዴግ እህት እና አጋር ድርጅቶች ለመዋሃድ የጀመሩት እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ እንድትወጣ የሚያግዝ ነው፡፡ የሀሳብ ብዝኃነት ለማስተናገድ እና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠርም እስካሁን ካለው የኢህአዴግ አካሄድ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ፡፡ በሀገሪቱ በስፋት ለሚስተዋሉት ብሔር ተኮር ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችልም ነው ምሁራኑ የተናገሩት፡፡

‘ውህደቱ አሀዳዊ ስርዓትን ለመመለስ የሚደረግ ጥረት ነው’ የሚል አስተያዬት የሚሰጡ የፖለቲካ ቡድኖች ዘመኑን የማይመጥን አመክንዮ ማቅረባቸውን ሊረዱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የፖለቲካ ምሁራኑ ውህደቱ አሀዳዊነትን የሚያነገስ ሳይሆን እውነተኛ ፌዴራሊዝምን የሚያጎናጽፍ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡ ‘አሀዳዊነት በሀገሪቱ ሊነግስ ነው’ የሚሉ አካላት የተሳሳተ “ፕሮፖጋንዳ” በመንዛት የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ያቀረቡት ደካማ አመክንዮ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

“አሀዳዊነት የአንድ ብሔር፣ የአንድ ቋንቋ እና የአንድ ሀይማኖት የበላይነት እንዲኖር ማድረግ ማለት ነው፤ በቀረበው የውህደት ሀሳብ ላይ ደግሞ ይህንን የሚያሳዩ ምንም ዓይነት ምልክቶች የሉም፤ ይልቁንም ለእኩልነት፣ ፍትሀዊነት እና ለሀሳብ ብዝኃነት እስካሁን ከነበረው የኢህአዴግ አካሄድ የተሻለ ይሆናል” ብለዋል ምሁራኑ፡፡
ኢህአዴግ ለዘመናት የተጓዘበት መንገድ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ የሚመልስ ባለመሆኑ አሠራሩን ለመቀየር የሚያደርገው ጥረት ጥሩ መሆኑን በዚህ አዲስ አካሄድ ላይ የፖለቲካ የበላይነታቸውና ጥቅማቸው የተነካባቸው ቡድኖች እና ደጋፊዎቻቸው አሳማኝ ያልሆነ አመክንዮ ማቅረባቸው ደግሞ ተገቢነት የሌለው የፖለቲካ አሰላለፍ እንደሆነንም አብራርተዋል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ሕዝብን ከማቀራረብ ይልቅ ማራራቅ ላይ ያተኩራል ያሉት ምሁራኑ የርዮተ ዓለም ለውጥ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩ ተመሳሳይ አላማ በመያዝ በተመሳሳይ ስርዓት ውስጥ ሆነው ሀገርን ለዓመታት ሲያስተዳድሩ የነበሩ ድርጅቶች ተመሳሳይ አቋም አለመያዛቸው አንዱ የውህደቱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ችግሮቻቸውን በውስጥ አሠራር እና በውይይት መፍታት ሲገባቸው ተቃራኒ የፖለቲካ ፓርቲ እስኪመስሉ ድረስ ሊታረቁ የማይችሉ አስተሳሰቦችን በመያዝ በአደባባይ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው ትክክል አለመሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በውይይት ሕዝበን ሊጠቅም ወደሚችል መንገድ መግባት እንደሚገባም መክረዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ደግሞ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት እየተነሱ ያሉ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበትን መንገድ ከውህደቱ በፊት ቀድሞ ማመቻቸት እና ጠንካራ ድርድር ማድረግ እንዳለበትም ምሁራኑ አስገንዝበዋል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከልም የወሰን እና የማንነት፣ ህገ መንግስት የማሻሻል፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የፖለቲካ ውክልና በምን መልኩ ሊመለሱ እንደሚችሉ ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ጥያቄዎቹ ከውህደት በኋላ የመመለስ እድላቸው አናሳ በመሆኑ ከዚያ በፊት ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ አዴፓ ጠንካራ ድርድር ማድረግን ትኩረት እንዲሰጠውም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleተዘግተው የነበሩ መንገዶች ክፍት እየተደረጉ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
Next articleድሬዳዋ እንድትረጋጋ መንግሥት አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡