
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ትናንት መንገድ በመዘጋቱ እየተጉላሉ የነበሩ መንገደኞች ሌሊት አዲስ አበባ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ትናንት ከአማራ ክልል ተነስተው በደጀን መስመር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያሉ ሱልልታ አካባቢ መንገድ ተዘግቶብን ለዕንግልት ተዳርገናል በማለት ለአብመድ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ተጓዦች ሌሊት አዲስ አበባ በሰላም መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የዐይን እማኞች እንደነገሩን ከሌሊቱ 6፡00 ገደማ በመከላከያ ሰራዊት ታጅበው ነው አዲስ አበባ የገቡት፡፡ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተነስተው ትናንት ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ሱሉልታ አቅራቢያ ሲደርሱ እንዳያልፉ በመደረጋቸው ከከተማው በቅርብ ርቀት በሚገኝ ሜዳ ላይ ሰፍረው እስከ እኩለ ሌሊት እንደቆዩም ነው የተናገሩት፡፡
ከ85 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እጀባ ተደርጎላቸው ወደ ከተማዋ እንደገቡም ነው የዐይን እማኝ መንገደኞቹ ለአብመድ የተናገሩት፡፡ በሌላ በኩል አዳራቸውን ገርበ ጉራቻ አድርገው ከንጋቱ 10፡30 ገደማ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ የጀመሩት መንገደኞች ደግሞ ጫንጮ ከተማ ላይ ቆመዋል፡፡ ሱልልታ ከተማ ላይ መንገድ ተዘግቷል በሚል ስጋት ነው ከ6 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ጫንጮ ላይ መቆማቸውን መንገደኞቹ ዛሬ ጠዋት የተናገሩት፡፡
አብመድ ስለጉዳዩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን በስልክ አነጋግሮ ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከየትኛውም አካባባቢ ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች ዛሬ ለተሽከርካሪዎች ክፍት እየተደረጉ ነው፡፡ የኮሚሽኑ የፖሊስ አባል እንደተናገሩት አሽከርካሪዎችም ሆኑ ተጓዦች የትናንቱን ክስተት መነሻ በማድረግ ስጋት ውስጥ ስለገቡ እንጂ በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ከትናንቱ የተሻለ አንፃራዊ መረጋጋት አለ፡፡ ስጋቱ የፈጠረው ድባብም በየአካባቢዎች የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን አመላክተዋል፡፡ ሁከት በነበረባቸው አብዛኞቹ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎችም ዋና ዋና መንገዶች ክፍት እየተደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ችግሩ አክቲቪስት ጃዋር ሙሃመድ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሆነ የስጋት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ የተፈጠረ መሆኑን ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም መከሰቱ ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ