
ባሕር ዳር: ሕዳር 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡ በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሀገር ለሚገቡ ሸቀጦች ወጪ ታወጣለች፡፡
በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ወደሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የታገዱት ሸቀጦች ላይ ውሳኔ የተላለፈው ለሀገር ውስጥ ምርት እድል ለመስጠት መሆኑን ተናግረዋል።
እገዳ የተጠላባቸው ምርቶች ሙሉ ለሙሉም ባይሆንም ለጥቁር ገበያ የተጋለጡ ናቸውም ብለዋል፡፡
የታገዱት ሸቀጦች መሠረታዊ ባለመሆናቸው መወሰኑንም አስታውቀዋል፡፡ በተወሰነው ውሳኔ እንደ ሀገር ከሚታጣው ይልቅ የሚገኘው ጥቅም እንደሚበልጥም ገልጸዋል፡፡ “ውስኪ ከማስገባት ማዳበሪያ ማስገባት ይሻላል” በሚል የተወሰነ ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ የመሬት ሀብት አያያዝ በተመለከተ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት የደላሎችና የሌቦች ሹመኞች መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ላይ ያለውን አካሄድ ከመሠረቱ ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
መሬት የሕዝብና የመንግሥት ኾኖ ሳለ የደላሎች እና የሌባ ሹመኞች መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
ቢያንስ በከተሞች መሬት የግለሰቦች መሆን መቻል አለበትም ብለዋል፡፡
በሕገወጦች ምክንያት በርካታ ሥራዎችን መሥራት አለመቻሉንም አስታውቀዋል፡፡ በኢንቨስተሮች ላይም ችግር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል መንግሥት እየሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!