
ሰቆጣ፡ ሕዳር 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዝቋላ ወረዳ ቅዳሚት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ የጎንደርና የአከባቢው ተወላጆችና ወዳጅ ኢትዮጵያዊያን 150 የመማሪያ ወንበር ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን ይዘው የመጡት አቶ አብልኝ ሙሉ አሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን 900 ሺህ ብር ወጭ በማድረግ 150 የተማሪዎች መማርያ ወንበር ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
በዋግ ኽምራ አካባቢ በጦርነቱ መጠነ ሰፊ ጉዳት የደረሰ በመኾኑ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የትምህርት መምሪያ ባለሙያ አቶ ወንድሙ አየነው ዋግ የጦርነቱ ዋና አውድማ በመኾኗ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን በመግለጽ የጎንደር አካባቢ ዲያስፖራዎች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ ችግሩ ሰፊ በመኾኑ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዋግ ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ባምላኩ አለቤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ዋግ በጦርነቱ በሁሉም ዘርፍ በሁሉም ወረዳዎች ሰፊ ጉዳትና ውድመት የደረሰ በመኾኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲደግፍ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
