
ባሕር ዳር: ሕዳር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፍቅር እና አብሮነት ሸማ ቢሆኑ ፈትላ የሰራቻቸው፤ አዳውራ የሸመነቻቸው ከተማ ደሴ ናት፡፡ ፍቅር እና ሰላም የአብሮ መኖር ጥበብ ከሆኑ የጥበብ አንጥረኛዋ ከተማ የቀድሞዋ ላኮመልዛ የአሁኗ ደሴ ናት፡፡ ፍቅር እና መቻቻል ኩታ እና ጋቢ ተደርገው ቢደረቡ የደማቅ ጃኖ ተምሳሌቷ ደሴ ሆና ትታያለች፡፡ እንግዳ ተቀባይነት እና ሰው አክባሪነት የአብራክ ክፋይ እና የአብሮነት ዘር ብቃይ ተደርገው ቢወሰዱ ያለጥርጥር ተምበርክካ እና አምጣ የወለደቻቸው፤ ዘርታ ያበቀለቻቸው ደሴ መሆኗ አይካድም።
ደሴ ኢትዮጵያዊነትን በጉያዋ ጠቅልላ እና አቅፋ የያዘች፣ ኢትዮጵያዊ ብዝሃነትን በነባር እሴቶቿ ያስመሰከረች እና በኢትዮጵያ ልክ ተሰርታ የጸናች ድንቅ ከተማ ነች፡፡ ደሴ ሆደ ሰፊ እና በብዙ ነገሯ ምሉዕ የምትባል ከተማ ናት። ደሴ ያለማጋነን ትንሿን ኢትዮጵያ ትወክላለች። ደመ ግቡዋ የደሴ ከተማ ደመ ግቡ ነዋሪ ይበዛባታል፡፡ ዛሬ ላይ እስላም ክርስቲያኑ፤ ደረሳ ካህኑ፤ አዛውንት ህጻኑ በፍቅር ተቀኝቶ በአብሮነት ተገርቶ የሚኖርባት ከተማ ጥሩ ከተባለ ብቁ ምሳሌ ሆና የዘለቀችው ግንባር ቀደም ከተማ ደሴ ናት።
ደሴ ክራር ሆና ብትሰደር በገና ሆና ብትደረደር፤ ቅኔ ሆና ብትቀኝ ስንኝ ሆና ብትሰኝ፤ የዜማ ቅኝቷ፣ ጥዑም ስልተምቷ እና ወርቁ ማንነቷ ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ ሰላም እና አብሮነት ናቸው። በመስጅዶቿ አዛን የሚሰማባት፣ በቤተ ክርስቲያኖቿ ወንጌል የሚሰበክባት እና በጎዳናዎቿ ፍቅር የሚቀነቀንባት ደሴ ዛሬም ድረስ የቀድሞውን ኢትዮጵያዊ አንድነት እንደጠበቀች ዘልቃለች። ከወደየት መጣችሁ ሳይሆን እንኳን ደህና መጣችሁ፤ የማን ናችሁ ሳይሆን እንዴት ከረማችሁ የደሴዎች ስሪት እና እምነት ነው። ደሴ የቀደመው የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ሰላም እና አብሮነት ህያው ሙዚየም ናት።
ልዩነት ላናወዘው፣ ጥላቻ ለመረዘው እና ግለኝነት ላደነዘዘው ዓለም ደሴነት ፍቱን መድኃኒት ናት። የውበት ሰገነቷ፤ የፍቅር ተምሳሌቷ ደሴ ለዓለም አብሮነት ልዩ ትምህርት ቤት ትሆናለች። ፍትህ በተዛባበት፣ ፍቅር በከሰመበት እና በደል በበዛበት ዓለም ውስጥ ደሴ የፍትሕ ጉባኤ እና የፍቅር ሱባኤ የሚስተናገድባት ከተማ ናት። ደሴ በፍቅር አጥምቃ፣ በይቅርታ አለቃልቃ እና በመቻቻል አርቃ ታወጣለች። ደሴ የፍቅር ስብራት ወጌሻ፤ የልዩነት ተውሳክ ማርከሻ የሆነች ከተማ ናት።
ደሴ የማራኪ ጭሷ ማዕዛ ከሩቅ ያውዳል፤ ሕዝቧ እንግዳን በፍቅር ተቀብሎ ያለምዳል፡፡ ለደሴ የጦሳ ተራራ ግርማ ሞገሷ፣ የአዘዋ ገደል ዋሷ፣ የጀሜ ተራራ ደግሞ ልብሷ ናቸው፡፡ ገራዶ እንደ መቀነት ጠምጥሟታል፤ ፒያሳ ደግሞ እንደ አምባር አድምቋታል፡፡ በእርግጥም ደሴን ተፈጥሮ እና ሰው ጠብ እርግፍ ብለው፤ ሃር እና ወርቅ ሆነው ያስማሟት ሕብረ ብሔራዊት ከተማ ናት፡፡
በተራሮች የተከበበችው ደሴ በኢትዮጵያ ቀደምት ፖለቲካ፣ እምነት፣ ታሪክ እና ባህል ውስጥ ከተራራ የገዘፈ እና አይረሴ ገናና ሥም እና ዝና አላት። የወሎየዎች መናገሻ፣ የአማራዎች መጠንሰሻ ደሴ ቀደምት የኢትዮጵያዊነት መዳረሻም ናት። ለሰማይ እና ለምድር የከበዱ ካህናቶች፤ ቃላቸው የማይታጠፍ መሻኢኮች መብቀያቸው የደሴ አድባር ነው። ለኢትዮጵያ ሰላም መሆን የፍቅር ገምቦዋ፤ የአብሮነት ማሰሮዋ የሚዘነበለው ደሴ ከተማ ነው።
በግንባታ ጥበባቸው የተለዩት ጥንታዊ ሰፈሮቿ የደሴን ቀደምት ከተሜነት ያሳብቃሉ። ደሴ ቀድማ ሰልጥና፤ ቶሎ ዘምና ለሌሎቹ መሰልጠን እና መዘመን አርአያ ሆናለች ሲባል ምክንያቶቹ የበዙ ናቸው።
አጼ ቴዎድሮስ የግዛት ወሰናቸውን ለማስፋት ወደ አካባቢው ሲዘምቱ ጀሜ ተራራ ላይ ጦራቸውን አስፍረው እና ድንኳናቸውን ተክለው በስስት የተመለከቷት ላኮመልዛ ቀልባቸውን በፍቅር እንደሳባቸው ይነገራል። የቀድሞው ላኮመልዛ ደሴ የሚለውን አዲሱን ስያሜዋን ስለማግኘቷ በርካታ አፈ ታሪኮች ቢኖሩም ከእነዚህ መካከል አንዱ አጼ ቴዎድሮስ በጀሜ ተራራ የተከሏት ድንካን መጠሪያዋ “ደስታ” ከመባሏ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው የሚሉ አሉ።
አጼ ዮሐንስ ለመናገሻ የተመኟት፣ አጼ ምኒልክ በፍቅር የወደቁላት እና አጼ ኃይለ ሥላሴ አሻራቸው ያረፈባት ደሴ የከተማነት ጠንሳሿ እና ቀያሿ ግን ንጉስ ሚካኤል ናቸው። ደሴ ከንጉስ ሚካኤል እስከ ወይዘሮ ሰኂን፤ ከእቴጌ መነን እስከ መምህር አካለ ወልድ የበዙ ባላሻራ ባለቤቶች አሏት። ደሴ ከአይጠየፍ የግብር አዳራሽ እስከ መርሆ ቤተ መንግሥት፤ ከደሴ ሙዚየም እስከ ወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ጎብኝዎችን የፍቅር ምርኮኛ፣ የትዝታ እስረኛ እና የስሜት ቁራኛ የማድረግ አቅም ያላቸው የመስህብ ቦታዎች አሏት።
የኢትዮጵያ መከራ እና ፈተና ሁሉ ሲፈትናት የኖረችው ደሴ በቅርቡ የነበረው ወረራ እና ጦርነትም ዘርፈ ብዙ ጉዳት አድርሶባታል። የደሴ ሙዚየም ተዘርፏል፣ አገልግሎት ሰጭ ተቋማቷ ተጎድተዋል። እንዲሁም ሆቴሎቿ ተመዝብረዋል። ከሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቷ እና ውድመቷ ገና ያላገገመችውን ደሴን መልሶ ለመገንባት ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ኅላፊ ትዕግስት አበበ ነግረውናል።
ደሴ ተደጋግፎ ለማደግ እና ተያይዞ ለመበልጸግ ተምሳሌት የሆነች ከተማ ናት ያሉን መምሪያ ኅላፊዋ ለዚህ ማሳያዋ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ አንዱ ነው ብለውናል። ነገር ግን በአዘዋ ገደል ለመገንባት የታሰበው አቋራጭ፣ አማራጭ እና ማሳለጫ (ሃይ ዌይ) መንገድ ግንባታ ሊታሰብበት እና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት። ከጦርነት ማግስት ከተማዋን መልሶ ለመገንባትም የባንክ እዳ ላለባቸው ሆቴሎች አማራጭ መፍትሄ መፈለግ እና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መጠገን ትኩረት ይሻልም ብለዋል።
ለከተማዋ መነቃቃት የክልሉ መንግሥት ልዩ ልዩ ሁነቶችን እያዘጋጀ ነው ያሉት መምሪያ ኅላፊዋ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የ12ኛ ክፍል ፈታኝ መምህራን የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ እንዲጎበኙ መደረጉ የከተማዋን ገጽታ በመገንባት በኩል ሚናው የጎላ ነበርም ብለውናል። ዘረፋ እና ውድመት የደረሰባቸውን የቱሪስት መዳረሻዎች ተጠንቶ ለክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የድጋፍ ማፈላለጊያ እቅድ ተልኳል ነው ያሉት።
በተረፈ ግን ደሴን መጎብኘት ታናሿን ኢትዮጵያን መመልከት ነው ያሉት ኅላፊዋ ዘመን ተሻጋሪ አብሮነት፣ ሕብረ ብሔራዊ ውበት እና ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት የከተማዋ ልዩ ተሰጥኦዎች ናቸው ብለዋል። እኛም ደሴን በመጎብኘት ኢትዮጵያዊ ውበትን ይሸምቱ እንላለን።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!