“የአምቦ ዮኒቨርሲቲ ለአንድ አመት ያስተላለፈው ቅጣት ተገቢ አይደለም፡፡” የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፡፡

166

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) “አሁን የተሰጠው ውሳኔ ያለፋቸውን ትምህርትና ፈተና እንዲወስዱና ተገቢው እውቀት እንዲኖራቸው እንጂ በሌላ ጥላቻ ወይም በተለየ ሁኔታ የተላለፈ አይደለም::” የአምቦ ዮኒቨርሲቲ

ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታቸው የታገዱ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውሳኔው ተገቢ አይደለም በማለት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
በአምቦ ዮኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተማሪ መካሻው ጌታ ለአብመድ እንደተናገረው በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በግቢው ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም በተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር አስታውሷል፡፡ የተፈጸመው ጥቃት ብሔር ተኮር መሆኑን በመገንዘብም ተማሪዎች በመነጋገር በወቅቱ ከግቢው እንደወጡ ነው የተናገረው፡፡ “በወቅቱ 830 ተማሪዎች ጊዜያዊ መልቀቂያ ቅፅ በመሙላት እንድንወጣ ዩኒቨርሲቲውን ብንጠይቅም አልተፈቀደልንም” ያለው ተማሪ መካሻው ጉዳዩ የዩኒቨርሲቲው ህግ ከሚፈቅደው በላይ በመሆኑ የመልቀቂያ ቅፅ ማስሞላት አንችልም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግሯል፡፡

ጥቃት እንደተፈጸመባቸውም ህይዎታቸውን ለማትረፍ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደነበር ነው የተናገረው፡፡ “ችግሩ በጥቂቱም ቢሆን ከረገበ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው ስንመለስ ሁላችንንም በአንድ ብሎክ አስቀመጡን፤ ምግብ እስከመከልከልና በቀን አንዴ እስከመመገብ ደረጃ ደረስን፤ የሰላሙ ሁኔታ አስጊ ስለነበር በዩኒቨረሲቲው ለሚመለከታቸው መሄድ እንደምንፈልግ ተናግረናል፤ አስፈላጊውን ጥበቃ እናደርግላችኋለን የሚል ምላሽ ከዩኒቨርሲቲው ከተሰጠን በኋላ ውጥረቶች በመኖራቸው ለመውጣት ተገደድን” ብሏል ተማሪው፡፡ ከሰኔ 5/2011 ዓ.ም ጀምሮ ችግሩ እንደከፋ የተናገረው መካሻው የማጠቃለያ ፈተና ሳይወስዱ መውጣታቸውንም ነግሮናል፡፡

በዚህ ኣመት ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው በየትምህርት ክፍላቸው ማመልከቻ ሲያስገቡ የዩኒቨርሲቲውን ሰራተኞች ይቅርታ እንዲጠይቁ መጠየቃቸውን፣ ይቅርታ መጠየቃቸውንም ነግሮናል፡፡
ሆኖም ጥቅምት 7/2011 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ላይ በወጣ ማስታወቂያ የአንድ ዓመት ቅጣት እንደተላለፈባቸው በመግለጽ ጥቅምት 8/2011 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ለቅቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን ነው ተማሪ መካሻ እና ሌሎችም ቅሬታ አቅራቢዎች የተናገሩት፡፡

የተላለፈው ቅጣት የተወሰኑ ተማሪዎች ማንነት ላይ ያነጣጠረ አለመሆኑን የተናገሩት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ግቢ ዲን ወይሳ አራርሳ ውሳኔው በዩኒቨርሲቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት 2ኛው ወሰነ ትምህርት ላይ ማጠቃለያ ፈተና ያልወሰዱ ሁሉም ተማሪዎች በዚህ ዓመት በ2ኛው ወሰነ ትምህርት ላይ ወደ ዩኒቨርሲቲው መጥተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የተላለፈ ነው ብለዋል፡፡

“ተማሪዎቻችንን እንደ ቤተሰብ ነው የምንከታተላቸው” ያሉት የቴክኖሎጂ ግቢ ዲን ወይሳ አራርሳ ችግሮችም ካሉ ለመፍታት ዝግጁ እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡ ተማሪዎቹ ይቅርታ እንዲጠይቁ በዩኒቨርሲቲው እንዳልተጠየቁም ዲኑ ተናግረዋል፡፡ አሁን የተሰጠው ውሳኔ ያለፋቸውን ትምህርትና ፈተና እንዲወስዱና ተገቢው እውቀት እንዲኖራቸው እንጂ በሌላ ጥላቻ ወይም በተለየ ሁኔታ እንዳልሆነም ነው የተናገሩት፡፡

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ጉዳይ ዳሬክተር አቶ ብርሃኑ ደጀኔ ተማሪዎች አነጋግረዋቸው እንደነበርና ተፈጻሚ የሆነው የዩኒቨርሲቲው ህግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleየጸጥታ ችግሩን ተከትሎ መንገድ ተዘግቷል፤ መንገደኞችም ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
Next articleተዘግተው የነበሩ መንገዶች ክፍት እየተደረጉ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡