ጎብኚዎች ናፍቀዋት የከረመችው ላሊበላ!

213

ባሕር ዳር: ሕዳር 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የበርካታ ጎብኚዎች የዓይን ማረፊያና መዳረሻ የነበረችው ላሊበላ በገጠማት ተደራራቢ ችግር እንግዶች ናፍቀዋት ሰነባብተዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ጦርነት እና የመብራት ችግር እንግዶቿ እንዳይመጡ አድርገውባት ቆይተዋል፡፡ ለወትሮው እንግዳ ሳትቀበል ውላ የማታውቀው ላሊበላ በደረሰባት ችግር እንግዳ ናፍቋት ከርሟል፡፡ ነዋሪዎቿም የእንግዶቿን መምጣት እየጠበቁ በር በሩን ሲያዩ ኖረዋል፡፡

ከጎብኚዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በጎብኚዎች መቅረት ከፍተኛ ችግር አጋጥሟቸው ነበር፡፡ የኮሮና ቫይረስ ቀንሶ፣ የጦርነት ስጋት እርቆላትም በመብራት እጦት ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ተቸግራ ቆይታለች፡፡ በጨለማ ውስጥ ኾና እንግዶቿን ስትናፍቅ ሰነባብታለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አጥልቶባት የነበረውን ጨለማ የሚገፍፍ መብራት አግኚታለች፡፡ ይህም ለከተማዋ ከፍተኛ ተስፋ ይዞ መጥቷል፡፡ ናፍቃው የነበረውን እንግዳም ማየት ጀምራለች፡፡

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የባሕልና ቱሩዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ላሊበላ የዓለም ዓይኖች የሚያርፉባት ዓለም አቀፍ ከተማ መኾኗን ገልጸዋል፡፡ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ከኢትዮጵያ አልፈው የዓለም አቀፍ ቅርስ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ላሊበላ የምጣኔ ሃብቷ መሠረት ቱሪዝም እንደኾነ ያነሱት ዲያቆን አዲሴ ቀደም ሲል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማስቀጠል የፀጥታ ችግር እና የመብራት እጦት ከተማዋን ሲፈትኗት ቆይተዋል ብለዋል፡፡ በኮሮና ቫይረስ እና በጦርነቱ ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ ቆሞ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ በፊት በዓመት ከ39 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ ይመጡ እንደነበር ያስታወሱት ዲያቆን አዲሴ በኮሮና ቫይረስ፣ በጦርነቱ እና ጦርነቱን ተከትሎ በመጣው ስጋት ጎብኚዎች እንደቀሩ ነው የተናገሩት፡፡ ከተማዋ ከወረራ ነጻ ከኾነች ወዲህ ጥቂት የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የመጡ ቢኾንም ከወትሮው ጋር ሲነጻፀር እዚህ ግባ የማይባል መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ሰላም ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ቀዳሚው ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ከተማዋ በጨለማ ውስጥ መቆየቷም ጎብኚዎች እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥሮባት ቆይቷል ነው ያሉት፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቀነሱ በከተማዋ ማኅበረሰብ ከፍተኛ የኾነ ጉዳት ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝም ጥገኛ የኾነው ማኅበረሰብ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መዝለቁንም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ከተማዋ ከጨለማ ወደ ብርሃን ተመልሳለች ያሉት ዲያቆን አዲሴ የሰላም ስምምነቱ እና መብራት መለቀቁ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋልም ብለዋል፡፡ መብራት ከመምጣቱ ማግሥት ከተማዋን ወደ ቀደመ የቱሪዝም እንቅስቃሴዋ ለመመለስ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አሁን በሚፈለገው ልክም ባይኾን የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እየመጡ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

በመብራት እና በውኃ አቅርቦት ችግር ተዘግተው የነበሩ ሆቴሎች ወደ ሥራ ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ሆቴላቸው የተዘረፈባቸው ባለሀብቶችም ሥራ እንዲጀምሩ ግብዓቶችን ለማሟላት እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

መብራቱና የሰላም ስምምነቱ በከተማዋ ታላቅ ተስፋ መጣሉንም ተናግረዋል፡፡ በቱሪዝም እንቅስቃሴ መዳከም ጫማ ከሚያስውቡት ጀምሮ በቱሪዝም ቀጥተኛ ተጠቃሚ የኾኑ አካላት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ከተማዋ በ2013 በጀት ዓመት ከ210 ሚሊዬን ብር በላይ ከቱሪዝም እንቅስቃሴ ሃብት አግኝታ እንደነበር ያነሱት ዲያቆን አዲሴ በ2014 በጀት ዓመት ወደ 14 ሚሊዬን ብር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ የገቢ መጠኑ ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የኾነ ማሽቆልቆል እንደገጠመውም ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ወደ ቀደመው እንቅስቃሴ ለመመለስ ላሊበላን ለማያውቁ የማስተዋወቅ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ታላቁን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከተማዋ ከደረሰባት ጉዳት በቶሎ እንድታገግም በቁጭት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ እንግዶች ወደ ከተማ ሲመጡ ጥሩ ጊዜ እንዲኖራቸው እና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዘም በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የመብራት ኀይል አገልግሎት ከተለቀቀ ወዲህ በከተማዋ ከፍተኛ ደስታ እንዳለም ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ተስፋ ሰጪ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

ከተማዋ ፍጹም ሰላም ናት ያሉት ዲያቆን አዲሴ መሠረተ ልማቶቿን ወደ ነበረበት የመመለስ ሥራ እየተሠራ በመኾኑ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ መጥተው ታላቁን ሥፍራ መጎብኘት አለባቸውም ብለዋል፡፡ ላሊበላ ለሚመጡ እንግዶች እንደተለመደው እጆቿን ዘርግታ እንደምትቀበልም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleቺርቤዋ ትክምቲ 30 ጌርክ 2015 ምሬት አሜታ
Next article“የፍትሕ ጉባኤ፤ የፍቅር ሱባኤ የሚስተናገድባት ከተማ!”