ʺታሪክ የሚቀዳባት፣ ቃል የሚጸናባት”

269
ባሕር ዳር: ሕዳር 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቀድማ አስቀደመች፣ ዘምና አዘመነች፣ ጸንታ አጸናች፣ አንድ ኾና አንድ አደረገች፡፡ ነገሥታቱ ለዙፋናቸው፣ ለግብር ማብያቸው፣ ለድንኳን መጣያቸው፣ ለቤተ መንግሥት መሥሪያቸው፣ ለሀገር ማዕከልነታቸው፣ ሊቃውንቱ ለሃይማኖት ማስተማሪያቸው፣ ለምስጢር ማመስጠሪያቸው፣ ለቤተ መቅደስ ማነጿያቸው፣ ደቀመዝሙራትን ለማፍለቂያቸው መረጧት፡፡ ነገሥታቱ የተዋቡ አብያተ መንግሥታትን ገነቡባት፣ ዙፋናቸውን አስቀመጡባት፣ አያሌ ታሪክ ሠሩባት፡፡
ሊቃውንቱ ደብር ደበሩባት፣ ገዳም ገደሙባት፣ ምስጢር አሜሰጠሩባት፣ ቀለም በጥብጠው ብራና ፍቀው ታሪክ ከተቡባት፣ ትርጉም ተረጎሙባት፣ ሥርዓት ሠሩባት፣ ደቀመዛሙርትን አፈለቁባት፣ ደቀመዛምርቱ የጥበብን እሸት ለመብላት፣ ከጥበብ ምንጭ ለመጠጣት ፈለጓት፣ በጉያዋ እየገቡ በገዳማቱና በአድባራቱ አጸድ ሥር እየተጠለሉ የጥበብን እሸት በሉባት፣ የጥበብን ውኃ ጠጡባት፡፡ የከበሩ መሻይኮች አረፉባት፣ በፍቅር ኖሩባት፣ ደረሳዎችን አስተማሩባት፤ ነጋዴዎች መዳረሻቸው ትኾን ዘንድ መረጧት፣ ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ሰንጥቀው ተጓዙባት፡፡ እስኪደርሱ ድረስ፣ ደርሰውም እስኪያርፉባት ናፈቋት፡፡ በደረሱም ጊዜ በደስታና በፍቅር ኖሩባት፣ ነግደው አተረፉባት፣ ወልደው ልጅ አሳደጉባት፡፡
ጀግኖች መወለጃቸው፣ ማደጊያቸው፣ መኖሪያቸው፣ ታሪክ መሥሪያቸው አደረጓት፣ ጠላቶች አፈሩባት፣ ወዳጆች አብዝተው ኮሩባት፡፡ ባማረው ቤተ መንግሥት ያማሩ ነገሥታት ተመላልሰዋል፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ ደራርበው ሠርተዋል፣ በአንድነት መክረው፣ በአንድነት ቃል ገብተው፣ በአንድነት ቃላቸውን አክብረው ሀገር አጽንተዋል፡፡ ጠላት አሳፍረዋል፡፡
ዓለም አጫዋቾች አብዝተው አዜሙላት፣ ባለቅኔዎች ተቀኙላት፣ ገጣሚዎች ስንኝ ቋጠሩላት፤ በአሻገር ያሉት አብዝተው ናፈቋት፡፡ ከአማረው ቤተ መንግሥት፣ ከተዋበው ቤተ መቅደስ ሥር ኾነው ታሪኳን ሊሰሙ ይጓጓሉ፡፡ ወደ እርሷ የሄዱት ጃን እያሉ በጃን ተከል ዋርካ ሥር ይጠለላሉ፣ በውበቱ ይዋባሉ፣ ታሪኩን ይመራሉ፡፡ ታሪክ ባደመቃቸው ጎዳናዎች እየተመላለሱ አጀብ ይላሉ፡፡
ጎንደር በታሪክ የደመቀች፣ በጀግኖች የተከበበች፣ በጃንተከል ዋርካ ጥላ የተዋበች፣ ዙሪያዋን በቆሙ ጌጠኛና ምስጢራዊ ተራራዎች ያጌጠች፣ ሰርክ አዲስ የሆነች ከተማ ናት፡፡ ዘምና እንዳለዘመነች፣ ከፍ ብላ ከፍ እንዳላደረገች ዛሬ ላይ ዘመኑን የዋጁ ልማቶች ቢርቋትም፣ ትናንት በሠራችው፣ ትናንት ባረቀቀችው ውበቷ እንደ ተዋበች ትኖራለች፡፡ በጉዛራ ያማረ ቤተ መንግሥቱን ጀምራ፣ በደንቢያና በደንቀዝ ውብ ሥፍራዎች አብያተ መንግሥታትን አሳምራ፣ በመናገሻዋ ከተማ ከጥበብ ላይ ጥበብ ደርድራ፣ ከውበት ላይ ውበት ደራርባ ደምቃ የምትኖር፣ ጀንበር ጠልቃ፣ ጀንበር በዘለቀች ቁጥር የምትሞሸር፣ ሰዎች ሁሉ ሙሽሪት፣ ንግሥት፣ አበቅየለሽ፣ ሰርክ አዲስ፣ እያሉ የሚጠሯት ውብ ከተማ ናት፡፡ በቤተ መንግሥቷ ኾና ጣና ሐይቅን በአሻገር እየተመለከተች፣ ግርማን እንደተላበሰች፣ ያያትን ሁሉ እንዳሳሳች ትኖራለች፡፡
ጣናን በአሻገር እያየች፣ ከገዳማቱና በአድባራቱ በሚወጣው ቅዱስ መንፈስ እየተባረከች፣ በሐይቁ ውስጥ ያለውን ያማረ ውበትና፣ የረቀቀ ምስጢር እየታዘበች የምትኖር መናገሻ ናት፡፡ የጎንደር ሊቃውንት ያለ ማቋረጥ ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባሉ፣ በጽናት የፈጣሪያቸውን ስም ይጠራሉ፣ ነጫጭ የለበሱ ምዕመናን ጎዳናዎችን አስውበው በሰርክ ወደ ቤተ መቅደስ ይጓዛሉ፣ በየአድባራቱና በየገዳማቱ ያማሩ ዜማዎች፣ ልብን በሀሴት የሚሞሉ ምስጋናዎች ይሰማሉ፣ የሚወጡት የምስጋና ድምጾች ከተማዋን ይባርካሉ፣ ይቀድሳሉ፣ ያስውባሉ፡፡ የጎንደር መሻይኮች አዛን ያደርሳሉ፣ ሳይሰለቹ በዱዓ ይተጋሉ፣ ለምድርም ሰላምና ፍቅር ይሆን ዘንድ ይማጸናሉ፡፡
ከማያልቀው ታሪኳ እየቀዳች፣ ለደረሰው ሁሉ እያጠጣች፣ በሰፊው እልፍኟ እንግዳ እየተቀበለች የምታስተናግድ ከተማ ናት፡፡ እንግዶቿን ጃኖ ታለብሳለች፣ ካባ ትደርባለች፣ በጠጅና በፍሩንዱስ ታቀማጥላለች፡፡ የመናገሻዋ ከተማ ሕያው ታሪክ፣ ምልክት፣ ብርታትና አንድነት ናት፡፡ ዛሬም መናገሻነቷን የሚያሳዩ፣ ሠረገላው የሚመላለስበት፣ ወይዛዝርቱ የሚወጡ የሚገቡበት፣ የጦር አበጋዞች በኩራት ሲራመዱ የሚታይበት፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ በክብር የሚኖሩባት፣ ነገሥታቱ ተውበው በዙፋን የተቀመጡባት ትመስላለች፡፡
ዛሬም በእልፍኙ ግብር የሚበላበት፣ ከአራቱም አቅጣጫ ወደ ቤተ መንግሥቱ ለግብር የሚገቡ ሰዎች የሚመጡበት፣ ሰረገላዎች፣ የጦር ፈረሰኞች የሚመላለሱባት ትመስላለች፡፡ ለምን ካሉ ግርማዋ እና ውበቷ አልጎደለምና፡፡
ያማረው ግርማዋ ዛሬም ከእነክብሩ አለ፡፡ ያማረው ቤተ መንግሥት ዛሬም እስከነ ውበቱ ይታያል፣ ሰፊው እልፍኝ፣ በጥበብ የተሠሩት ጥበባዊ በሮች ዛሬም ያያቸውን እያማለሉ ይኖራሉ፡፡ በአብያተ መንግሥታቱ ዙሪያ ያለ ምክንያት የተሠራ የለም፡፡ ሁሉም በምክንያት እና በረቀቀ ብልሃት ተሠሩ እንጂ፡፡
ጎንደር በታሪክ ከደመቁት፣ ከፍ ብለው ከተቀመጡት፣ ስልጣኔን ከሚያሳዩትና ከሚመሰክሩት ከተሞች መካከል ከግንባር ቀደሞቹ ጎራ ናት፡፡ የበዙ ጎብኚዎች ሊያዩዋት ይጓጉላታል፣ ከራቀ ሀገር እየተነሱ ይጓዙባታል፡፡
ʺማን ሀሰት ይለኛል እውነቱን ብናገር
የታሪክ አሻራው ዛሬም አለ ጎንደር” እንዳለች ከያኔዋ የታሪክ አሻራው ዛሬም በጎንደር ሰማይ ሥር ደምቆና አሸብርቆ አለ፡፡ ዘመን የማያስረጀው፣ የረቀቀ ነውና ዛሬም ደምቆ ይታያል፣ ዛሬም ተውቦ ይጣራል፡፡ የጎንደር ውበት በመላው ዓለም የሚገኙ ጎብኚዎችን እየሳበ ይጣራል፡፡ ጎንደር በዙሪያዋ አያሌ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስፍራዎች ከበዋታልና በጎብኚዎች ትመረጣለች፡፡ ቢያሻው ወደ ባለ ግርማው የራስ ደጀን ተራራ፣ ቢያሻው ወደ መተማና ቋራ፣ ቢያሻው ወደ ወልቃይት ጠገዴ ሑመራ፣ ቢያሻው ወደ ደንቢያና ፎገራ መሄድ የሚችሉባት ማዕከል የሆነች፣ ውበትን የተጎናጸፈች ናትና፡፡
በዘመነው ዘመኗ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አርቅቃ የያዘች፣ አንድነትን ያጸናች፣ ለሀገር ፍቅርና፣ ለሠንደቅ ክብር በብርታት የኖረች ከተማ ናት ጎንደር፡፡ ዛሬም አንድነት፣ ጽናት፣ ቃል አክባሪነት፣ ጀግንነት፣ እውነት፣ ኢትዮጵያዊነት መገለጫዋ ነው፡፡
ከመናገሻዋ ከተማ የደረሰ ሁሉ ልቡ በፍቅር ይቀልጣል፣ በአግራሞት ይዋጣል፡፡ የረቀቁ እጆች የተጠበቡባቸውን አብያተ መንግሥታት፣ እጹብ የሚያሰኙ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት፣ እንደ ጀግና ሰልፈኛ የቆሙ ተራራዎች፣ ታሪክ የሚዘክራቸው የከበሩ ቦታዎች እርሷን ውብ የሚያደርጓት ናቸው፡፡
ይሂዱና ይጎብኟት ታሪክና ጥበብ ይማሩባታል፣ ይሂዱና ይዩዋት ጀግንነት እና አንድነት ያዩባታል፣ ፍቅርና ክብር ይጎናጸፉባታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleʺስፖርት መዝናኛ ብቻ አይደለም፣ ስፖርት ኢኮኖሚም ነው” ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleበትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎች ማቅረብን ጨምሮ አገልግሎቶች ዳግም መጀመራቸውን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።