ʺስፖርት መዝናኛ ብቻ አይደለም፣ ስፖርት ኢኮኖሚም ነው” ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

193
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳርን ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ሁለተኛ ዙር ቀሪ ሥራዎችን ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
ሥራውን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ባሕርዳር ከተማ የተዋበችና የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የቱሪዝም ማዕከል ናት ብለዋል፡፡ ከተማዋ ከፍተኛ የኾነ የተፈጥሮ ጸጋ ያላት ናት ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ጸጋዋን አውጥተን ግን አላሳየናትም ነው ያሉት፡፡
ጸጋዋን መጠቀም ከተቻለ መላውን ዓለም መሳብና ወደ ከተማ እንዲመጣ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ እንደ ተፈጥሮ ውብነቷ ሀብቷን በአግባቡ አውጥቶ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ስፖርት መዝናኛ ብቻ አይደለም፣ ስፖርት ኢኮኖሚም ነው ብለዋል፡፡
ስታዲዬሙ ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ በመቆየቱ የአማራ ሕዝብ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ መጎዳቱን ተናግረዋል፡፡ ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ገንዘቡ ለሕዝብ ምንም እንዳልፈየደ መገንዘብ ይቻላልም ብለዋል። በየትኛውም አቅጣጫ የተጀመሩ ፕሮጄክቶችን ማጠናቀቅ የግድ አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
መጀመር ብቻ ግብ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ግቡ የተጀመረውን ሥራ ማጠናቀቅ መቻል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የተጀመሩ ፕሮጄክቶችን ማጠናቀቅ አለብን በሚል የክልሉ መንግሥት እየሠራ መኾኑንም ነው ያስረዱት፡፡ ስታዲዬሙ የፊፋን መሥፈርት አሟልቶ ጨዋታዎች እንዲካሄዱበት ለማድረግ ሥራውን አስጀምረናልም ነው ያሉት፡፡
ሁለተኛው ዙር የስታዲዬሙ ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾን እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ቀሪው ሥራ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ማጠናቀቅ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የስታዲዬሙ ግንባታ ለሀገር ትልቅ የለውጥ እርምጃ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ስታዲዬሙን የሚመጥን የሆቴል ቱሪዝም መስፋፋት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ ስታዲዬሙ መዝናኛና የምጣኔ ሃብት አቅም እንዲኾን እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡
በስታዲዬሙ ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሥፍራዎች በአግባቡ ተጠብቀው ለመዝናኛና ለስፖርት አገልግሎት ብቻ እንዲኾኑ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ ከባሕርዳር ባለፈ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ስፖርት እንዲስፋፋም እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የወልድያ ስታዲዬም ሥራ እንደሚጀምር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ስፖርት በኅብረተሰቡ እገዛ ማደግ ይገባዋልም ብለዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ቃላችን ማክበርና መጠበቅ ይገባናል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፡፡
መንግሥት ለስታዲዬሙ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡ በመንግሥት በኩል የሚቀመጥ ሰበብ እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ስታዲዬሙ ተጠናቆ ለአገልግሎት ብቁ ኾኖ ማየት እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡
በስታዲዬሙ ግንባታ የተሠማሩትም በአግባቡ ሠርተው ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡
ለስታዲዬሙ ግንባታ ድጋፍ ያደረጉትንም አመስግነዋል፡፡
ለስፖርቱ እድገት ሁሉም በሚችለው እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleʺማይካድራ ትታወሳለች፣ ሳትረሳም ትታሰባለች”
Next articleʺታሪክ የሚቀዳባት፣ ቃል የሚጸናባት”