
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደል ሳይገኝባቸው፣ ሐጥያት ሳይቆጠርባቸው በግፍ አልቀዋልና እናስባቸዋለን፣ የነገዋን ጀንበር ማየት እየጓጉ፣ በፍስሃና በደስታ መኖር እየፈለጉ በግፍ ሞተዋልና እናስባቸዋለን፣ ኮልታፋ አንደበት ያላቸው ልጆች ከአባታቸው እግር ሥር እየተሹለከለኩ አባቶቻቸውን እንዲምሩላቸው እየጠየቋቸው አሻፈረኝ ብለው ገድለውባቸዋልና እንዘክራቸዋለን፣ ሲራቡ አጉርሰው፣ ሲጠሙ አጠጥተው፣ ሲታረዙ አልብሰው፣ ሲታመሙ ዳስሰው የኖሩት በግፍ ተጨፍጭፈዋልና እናስታውሳቸዋለን፡፡
እናቶች እንባቸውን እያፈሰሱ ለመኗቸው፣ ባጠቡት ጡት ተማጸኗቸው፣ ልጆቻቸውን ይምሩላቸው ዘንድ አብዝተው አለቀሱ፣ እነርሱ ግን እያሳዩ ገደሉባቸው፣ ጧሪና ቀባሪ አሳጧቸው፣ በግፍ ደማቸው ስለፈሰሰ ወገኖች ስንል ስማቸውን እናነሳለን፣ የተሰውበትን ቀን እናስባለን፡፡
ስለ ተከበረች ማንነታቸው፣ እንከን ስለሌለባት እውነታቸው ሲሉ ሞተዋልና እንዘክራቸዋለን፡፡ የምናስታውሳቸውስ በምድር ጥላቻን እየሰበክን አይደለም የንጹሐን ደም በከንቱ እንዳይቀር ለማስታወስ እንጂ፣ የምንዘክራቸውስ ለበቀልም አይደለም በግፍ የፈሰሰችው ደም ክብር ስላላት እንጂ፣ የምናስባቸውስ ለጥልም አይደለም ስለ እውነት ያለፉትን ለማክበር ነው እንጂ፡፡ የምንዘክራቸውስ ስለ ከበረች ደማቸው፣ ስለ ማትሻር ቃል ኪዳናቸው፣ በግፍ ስላለቁባት ጭንቀታቸው ነው፡፡
ጥላቻ ባሰከረው ታጣቂ ቡድን ንጹሐን ተሰቃዩ፣ ነብሳቸው መድረሻ ሥፍራ፣ መጠጊያ ቦታ አጣች፡፡ አንገታቸው ለሰይፍ፣ ግንባራቸው ለጥይት አሩር ተዘጋጀች፡፡ በግፍ አዘጋጅተው፣ በግፍ ገደሏቸው፣ በግፍ ተነስተው በግፍ ጨፈጨፏቸው፡፡
ሞትስ ለሰው ዘር ሁሉ የተሠራች ናት፡፡ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀርባታል እንጂ አይርቃትም፣ አያመልጣትም፣ እጹብ ያሰኙት አበቦች ይረግፋሉ፣ እጅግ የተዋቡት ይጠወልጋሉ፣ ዝናቸው ከዳር ዳር የተሰማላቸው ይሞታሉ፣ በዘመናቸው ሥፍራ አልበቃቸው ያላቸው ጀግኖች በጠባብ መቃብር ይወሰናሉ፣ የወርቅ ጫማ የተጫሙት፣ የወርቅ ካባ የለበሱት፣ የአልማዝ ዘውድ የጫኑት፣ የወርቅ በትር የጨበጡት፣ በአማረ ሰረገላ የተጓዙት ሁሉ ያን ሁሉ ከምድር በላይ ትተው እነርሱ አፈር ይቀምሳሉ፣ እጅና እግራቸውን ታስረው ወደ መቃብር ይወርዳሉ፡፡
እስትንፋስን የሰጠ አምላክ በቃ ባለ ጊዜ እስትንፋስን ሲነጥቅ ተቆጭ የለውም፣ አንተው ሰጠህ አንተው ነሳህ ተብሎ ይታለፋል እንጂ፡፡ እርሱ የሠራትን እርሱ ሊያፈርሳት የተገባች ናትና ለምን እንዲህ አደረክ አይባልም፡፡ ለምን በሥራው ጣልቃ አይገቡበትምና፡፡ እርሱ አስውቦ የሰራቸውን፣ እርሱ ያከበራቸውን በጥላቻ የተነሱት ሲገድሏቸው፣ ሲያሰቃዩዋቸው፣ መድረሻ ሲያሳጧቸው ግን ከበደልም ይከፋል፣ ከክፋትም ይሰፋል፡፡
እኒያ በላባቸው ሰርተው የሚጉርሱት፣ እኒያ ጥረው ግረው የሚያጎርሱት ንጹሐንን በጥላቻ የተነሱት ገደሏቸው፣ የሚያዝኑትን ጨከኑባቸው፣ የሚራሩትን ስለት አሳረፉባቸው፡፡ ያቺ ብርቱዎች ለሥራ የሚጣደፉባት፣ ሥራ ወዳዶች የሚኖሩባት ከተማ የደም ጎርፍ ፈሰሰባት፣ የተጨነቀች ድምጽ ተሰማባት፡፡
በወረኃ ጥቅምት በ24ኛው ቀን ኢትዮጵያ ተዋጋች፣ ኢትዮጵያውያን አስደናጋጭ ወሬ ሰሙ፡፡ ዳር ድንበር የሚያስከብርላቸው፣ ከራስ በላይ ለሀገርና ለሕዝብ እያለ ከጠላት የሚከላከላቸው፣ በክብር የሚያኖራቸው፣ በጠላቶቻቸው ፊት ባለ ድል የሚያደርጋቸው ሠራዊት ተወግቷልና፡፡ በዚያች ሌሊት ብዙዎች ሞተዋል፣ ብዙዎች እርቃናቸውን ቀርተዋል፣ ብዙዎች ቆስለዋል፣ ብዙዎች በሞት መካከል ኾነው ውጊያ ገጥመዋል፡፡
ጠባቂው የተነካበት ሕዝብ በቁጣ ተነሳ፡፡ የተነካው ሠራዊትም የማይጨበጥ እሳት ኾነ፡፡ ከጀርባው የወጉትን ፊቱን አዙሮ ወጋቸው፣ አደብም አስያዛቸው፡፡ ቀናት ተቆጠሩ፣ ሠራዊቱን ከጀርባው ወግተው ወደ ፊት መገስገስ ያማራቸው መራመድ ተሳናቸው፡፡
ወረኃ ጥቅምት ተሰናብቶ ስልጣኑን ለወረኃ ኅዳር አሳልፎ ሊሰጥ የመጨረሻዋ ቀን ደርሳለች፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሲቲት ሁመራ ሰማይ ሥር የጀግኖችን ምት ያልቻለው ታጣቂ አንድ ዕቅድ ነድፏል፡፡ የነደፈው ዕቅድም ከአዕምሮ የማይጠፋ ክፉ ሥራ ነበር፡፡
ያቺን ምድር የደም ምድር ያደረጋት ዘንድ ወደደ፡፡ በንፁሐን ላይም ሰይፉን ሳለ፡፡ የማይካድራ ወገኖችን ለሞት አዘጋጃቸው፣ ገጀራም አዘጋጀላቸው፡፡ ጀግኖቹ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ንጹሐንን እያሳደደ ጨፈጨፋቸው፣ ዘራቸውን እየቆጠረ ደማቸውን አፈሰሰው፣ አጥንታቸውን ከሰከሰው፡፡ ማይካድራ ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰባት፣ የመከራ ድምጽ ተሰማባት፡፡ እነሆ የማይካደራ ወገኖች ያለቁባት፣ በግፍ የተሰውባት፣ በጭካኔ የሞቱባት ቀን ዛሬ ናት፡፡
ዓመታት አልፈው፣ ዓመታት ቢተካኩም፣ ዘመናት አልፈው ዘመናት ቢመጡም፣ ትውልድ አልፎ፣ ሌላ ትውልድ ቢመጣም ጥቅምት 30 ግን አትረሳም፡፡ ለምን በደል ያልተገኘባቸው ሞተውባታልና፣ ያቺ የከፋች ቀን ትታሰባለች፣ ትታወሳለች፣ ዳግም ሞት እንዳይኖርባት፣ ዳግም ስቃይ እንዳይመጣባት ትዘከራለች፡፡ ለትውልድ ስትነገር ትኖራለች፡፡
ስለ ፍቅር ይቅር ይላሉ፣ ስለ በደላቸው ግን ፍትሕን ይጠይቃሉ፣ ስለ ሰላም ሳያታክቱ ይሠራሉ፣ የደረሰባቸውን በደል ግን ያስታውሳሉ፣ በታሪክም ይመዘግባሉ፣ ስለ ፍቅር ይቅር ይላሉ ማንነታቸውን እና ክብራቸውን ግን ያስከብራሉ፡፡
ስለ ሀገር ይቅር ይላሉ እውነታቸውን ግን አጥብቀው ይይዛሉ፡፡ ስለ ሰላም ይቅር ይላሉ በግፍ የፈሰሰውን ደም ግን ይዘክራሉ፡፡ ማይካድራን ያስታውሳሉ፣ ነጻነታቸውን አብዝተው ይጠብቃሉ፣ የሀገራቸውን ወሰን ያስከብራሉ፡፡ ማይካድራ ላትረሳ ትታወሳለች፡፡ በደም ቃል ኪዳን ጸንታ ትኖራለች፡፡ በትውልዱ ልብ ውስጥ ተቀምጣለች፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!