የጸጥታ ችግሩን ተከትሎ መንገድ ተዘግቷል፤ መንገደኞችም ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡

174

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከአማራ ክልል ተነስተው በደጀን መስመር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ መንገደኞች መንገድ በመዘጋቱ ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ተናገሩ፡፡

መነሻቸውን ከአማራ የተለያዩ አካባቢዎች አድርገው በደጀን መስመር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ተጓዦች ለአብመድ እንደተናገሩት መንገድ በመዘጋቱ ለእንግልት እየተዳረጉ ነው፡፡ ተጓዦቹ የአማራ ክልል ከተሞችን አቆራርጠው ሱሉልታ እስኪደርሱ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሱሉልታ ላይ መንገድ በመዘጋቱ አሁን ካሉበት ቦታ እንዳያልፉ መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡

የዓይን እማኝ መንገደኞቹ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ከሱልልታ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ሜዳ ላይ ሰፍረው እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት፡፡ ሱሉልታ ላይ ስለተፈጠረው የመንገድ መዘጋት ችግር መፍትሔ፣ ለመንገደኞች መደረግ ስላለበት የህግ ከለላ እና ሌሎችም ጉዳዮች ለማነጋገር አብመድ የጸጥታ አካላትን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የክልሉ የፀጥታ ሀይሎችን ስለ ጉዳዩ ቢጠይቁም ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳላገኙም መንገደኞቹ ነግረውናል፡፡ አብመድ ስለጉዳዩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን ጠይቆ ነበር፡፡ ችግሩ በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች አለመረጋጋት በመኖሩ የተፈጠረ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡ የኮሚሽኑ የመረጃ ባለሙያ ኢንስፔክተር ደረጀ አሰፋ ለአብመድ በስልክ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በሻሸመኔ፣ በሀረር፣ በአዳማና በሌሎች አካባቢዎችም የፀጥታ ችግሮች መኖራቸውን ነው በማሳያነት የጠቀሱት፡፡

የፀጥታ ችግሩ አክቲቪስት ጃዋር ሙሃመድ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ጥቃት ሊደርስበት እንደሆነ የስጋት መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ የተፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ባለሙያው በአካባቢው ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን እንዲያረጋጉ አማራጭ መፍትሄ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይዎት ማለፉን፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም መከሰቱን ምንጮች እየገለጹ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Previous articleየቤተ እምነት እና የምዕመኖቿን ደኅንነት ለመጠበቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ቤተ ክርስቲያኗ አስታወቀች፡፡
Next article“የአምቦ ዮኒቨርሲቲ ለአንድ አመት ያስተላለፈው ቅጣት ተገቢ አይደለም፡፡” የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፡፡