የጥበብ ሰው ሽኝት!

137

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የተወለደው ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አቅጣጫ የመጡትን ወዳጆቿን በፍቅር፤ ጠላቶቿን ደግሞ አይበገሬነቷን አሳይታ በምትሸኘው ድሬድዋ ነው፡፡ የሰላም፣ የፍቅር፣ የእንግዳ ተቀባይነት እና የመቻቻል ተምሳሌት በኾነችው ድሬ 1940 ዓ.ም እንደተወለደ የሚነገርለት ታላቁ የሙዚቃ ሰው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በጥበቡ ዓለም ውስጥ አሳልፏል፡፡

ታላቁ የጥበብ ሰው ቤተሰቦቹ የሰጡት መጠሪያ ስም አሊ መሐመድ ሲኾን በበርካቶች ዘንድ የሚታወቅበት አሊ “ብራ” ግን ከሥራዎቹ ጋር በተያያዘ የተሰጠው መለያ ስም ነው፡፡ ከአንድ የሙዚቃ ሥራው ጋር በተያያዘ የተሰጠው ስያሜ እስከ እድሜ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ በብዙዎች ዘንድ መለያው እና መጠሪያው ኾኖ ዘልቋል፡፡

ቋንቋ ያልገደባቸው እና ስልተምት ያልለያቸውን የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎችን አዘውትሮ ሲያዳምጥ እንዳደገ የሚነገርለት ታላቁ የጥበብ ሰው አሊ ቢራ ወደ ሙዚቃ ሕይዎት የተቀላቀለው በትምህርት ቤት እና በቤቱ ለቤተሰቡ እና ለጓደኞቹ በማንጎራጎር እንደነበር ይነገራል፡፡ በአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ሥራውን የጀመረው አሊ በታዋቂው የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ የመጫወት እድልም አግኝቷል።

የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት የምስራቋ ፀሐይ ድሬድዋ ያበቀለችው አሊ ልክ እንደ ድሬድዋ እርሱም የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገራል፤ በተለያዩ ቋንቋዎችም ያቀነቅናል፡፡ ከአረብኛ እስከ ኦሮምኛ፤ ከአደሬኛ እስከ ሶማሊኛ አሊ እያፈራረቀ አቀንቅኖባቸዋል። ለሶማሌዎች ቅርብ፣ ለጅቡቲዎች ቤተኛ እና ለሱዳኖች የልብ ወዳጅ የኾነው ታላቁ የጥበብ ሰው ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በፍቅር ትዘልቅ ዘንድ የጥበብን አቅም ተጠቅሟል ይባልለታል፡፡

የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ ፍሬስብሃት አርቲስት አሊ ቢራን “ሙሉ የሙዚቃ ሰው” ሲል ይገልጸዋል፡፡ ግጥምና ዜማ ይደርሳል፣ ፒያኖ፣ ጊታርና ኡድ የመሳሰሉትን የሙዚቃ መሣሪያዎችንም ይጫወታል፣ ሙዚቃዎችን ያቀናብራል። ኢትዮጵያ ውስጥ በወርቃማዉ የሙዚቃ ዘመን ከተፈጠሩ የሙዚቃ ባለሞያዎች አንዱ የኾነው አሊ መሐመድ ቢራ ሥራዎቻቸው በቡዳ ሪከርድስ በኢትዮፒክስ ሲሪየስ ከታተሙላቸው ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች መካከልም አንዱ ነው።

አንድ ወቅት አሊ ቢራ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደተናገረው 267 እራሱ ያቀናበራቸው የሙዚቃ ሥራዎች አሉት። ለ56 ዓመታት ሙዚቃን እንደሙያ፣ ጥበብን እንደመለያ አድርጎ የተጫዎተው አሊ ሥራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ፍቅር፣ ነጻነት፣ አንድነትን እና መተሳሰብን በሙዚቃ ሥራዎቹ ሲሰብክ የኖረው አሊ በተለይም ሃቅን መስበክ እና ስለሃቅ ማቀንቀን የነፍስያ ስሪቴ ነው ሲል ተደምጧል፡፡

ኢትዮጵያዊ ኾኖ አፍሪካዊ ተጽዕኖ የፈጠረው እና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በተወዳጅ ሥራዎቹ የዘለቀው አሊ ቢራ ጉዞውን ጨርሷል፡፡ የጥበብን ሰው ሽኝት! በሚመጥን መልኩም እትብቱ ወደ ተቀበረባት ድሬ ድዋ ተሸኝቷል፡፡ ነፍስህ በሰላም ትረፍ፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleበኩር ጋዜጣ – ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም ዕትም
Next articleየሰላም ስምምነት ሂደቱ በኬኒያ መካሄድ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።