
ሁመራ: ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሠራዊት የተካደበትን ቀን ጥቅምት 24 ምክንያት በማድረግ ዝክረ ሰማእታት መርሃ ግብር በወልቃይት ጠገዴ ቃብቲያ ሁመራ ተካሂዷል።
በዝክረ ሰማእታት መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬም ‟የሞትነው እንደ ሀገር ነው፣ የተነሳነው እንደሀገር ነው፣ ትንሣዔያችን የጋራ ነው” ብለዋል።
ጥቅምት 24 መከላከያ ሠራዊት ሞትን ፊትለፊት ገጥሞ አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ፣ የኢትዮጵያ ትንሣዔ የተበሰረበት ዕለት በመኾኑ ሁሌም ታስቦ ይውላል ብለዋል ኮሎኔሉ።
ሂትለር ፈጽሞታል ከተባለው በላይ ግፍ የተፈጸመባችሁ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች ያ ቀን አልፎ ለዚህ በቅታችኋልና ደስ ይበላችሁ ብለዋል፡፡
የተዋጋነው የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥትን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተነሳው አጥፊ ቡድን እና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እንደኾነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ውጣውረዳችንን፣ ርሃባችንን፣ ሞታችንን፣ መስዋእትነታችንን፣ ድካማችንን ተሸክማችሁ ይዛችዃል እና ሞታችን ውጣውረዳችን ለእኛ ጌጣችን ነው ክበሩልን ብለዋል።
መስዋእትነት ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ኮሎኔሉ ሁሉም የሀገሩን ከፍታ ማረጋገጥ ይገባዋል ነው ያሉት።
ድህነትን ለማሸነፍና በኢኮኖሚ ለማደግ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ለሀገር ድንበር መከበር ከአራቱም መዓዘን የተውጣጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መስዋእትነትን ከፍለዋል፤ ለዚህም ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!