
ሁመራ: ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዝክረ ጥቅምት 24 በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቃብትያ ሁመራ እየታሰበ ነው፡፡
በዝክረ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እውነትን ይዞ የታገለ ሁልጊዜም አሸናፊ ነው ብለዋል፡፡ እውነትን ይዞ የታገለ አሸናፊ እንደሚኾንም እኛ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ምስክር ነን ነው ያሉት፡፡
የወልቃይት የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ፍጹም እውነት ነበርም ብለዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የሕወሃትን ግፍ በመቃወም ከፋኝ ብሎ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ቆይቶም በሕግና በሥርዓት ጥያቄውን ለማስመለስ የወሰን እና የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አቋቁሞ ሲታገል መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
ወያኔ በማይደፈርበት ዘመን ደፍሮ የሞገተ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራ ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ቢታሰርም ቢገደልም ከእውነትና ከዓላማው ዝንፍ ሳይል ኢትዮጵያዊና ማንነቱ ደግሞ አማራ ነኝ የሚል ነውም ብለዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በኢትዮጵያ ላይ አዲስ ለውጥ እንዲመጣ በር የከፈተ ጀግና ሕዝብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የመከላከያ ሠራዊትን ሲያጠቃ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሠራዊቱ ከተጠቃበት ጊዜ ጀምሮ ከሠራዊቱ ጋር አብሮ የቆመ ነው ብለዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ፣ ቤቴና ንብረቴ ሳይል ሀገርን እየጠበቀ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዓመታት ሀገርን የጠበቀ ጠንካራ ሕዝብ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ በጀት አለመመደብ እና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩበትም ችግሮቹን ተቋቁሞ መንግሥትን በማመን፣ በመታመን እና ከሠራዊቱ ጋር በመኾን ሀገሩን የጠበቀ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡ ጦርነቱ ወያኔን ብቻ ሳይኾን ጥንተ ጠላቶቻችን የውጭ ጠላቶች የተሸነፉበት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብ አሸናፊ ኾኖ ዘልቋልም ብለዋል፡፡
ዛሬ በነጻነት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም እያሰቡ እያከበሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ እውነትን ይዘን አሸንፈናልም ነው ያሉት፡፡
እውነትን ይዞ የታገለ ሁሌም አሸናፊ ነው፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ወደፊትም ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ወያኔን የተዋጋ፣ የተሟገተ ጠንካራ ሕዝብ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!