ʺያመኑት ከዳቸው፣ የጠበቁት ገደላቸው”

286
ባሕር ዳር: ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሕይወት ዋጋ ሀገር የሚጠብቀውን፣ ወገን የሚያኮራውን፣ ታሪክ የሚሰራውን ገደሉት፣ ለሀገር የታመነውን፣ ታምኖ የሚኖረውን፣ ለቃል ኪዳኑ የሚሞተውን ካዱት፣ ያጎረሰውን ነከሱት፣ ያለበሰውን በራቁት አስሄዱት፣ ሲጠማ ያጠጣውን ውኃ ነፈጉት፣ ሲቸግር ያስጠለለውን መጠለያ አሳጡት፣ በመከራ ዘመን ሕይወቱን፣ በደስታ ዘመን ጉልበቱን የሚሰጠውን ግፍ ፈጸሙበት፡፡
የእናት ሀገር አደራ የተቀበለውን፣ ሀገር በደምና በአጥንት የሚያጸናውን፣ ለሀገር ፍቅርና ክብር ሲል ራሃብና ጥሙን የሚችለውን፣ በምሽግ ውሎ በምሽግ የሚያድረውን፣ ለሠንደቅ ሲል ሞትን የሚንቀውን በጀርባው ወጉት፡፡
በጠበቃት ሀገሩ መቀበሪያ አሳጡት፣ አስከሬን በሚከበርበት ሀገር፣ አስከሬን ቆሞ በሚሸኝበት፣ ተለቅሶ በሚያርፍበት ምድር በግፍ ጎተቱት፣ ለወትሮ ሰው ሲሞት ይለቀሳል፣ እነርሱ ግን በሙታን መካከል ኾነው ከበሮ እየመቱ ደለቁ፣ በሙታን ተሳለቁ፤ በግፍ ገደሉት፣ ገድለው ጎተቱት፡፡
አምነውና ታምነው ለዓመታት ጠበቁት፣ ሞተው አኖሩት፣ ተርበው አጎረሱት፣ ተጠምተው አጠጡት፣ ታርዘው አለበሱት፣ መጠለያ ሳይኖራቸው መጠለያ ሠሩለት፡፡ አምኗቸዋልና ጀርባውን ሰጥቶ ወደ ፊት እያዬ ጠበቃቸው፣ አምኗቸዋልና እነርሱ በቅንጡ ቤት እየኖሩ እርሱ በምሽግ ተኝቶ ከለላቸው፡፡ አጥር ኾኖ አስከበራቸው፣ ጋሻ ኾኖ ከጦር አዳናቸው፡፡ እነርሱ ግን በበረሃ ውሎ በምሽግ እያደረ የከለላቸውን በተቀናጣ ቤት ውስጥ እየኖሩ ይገድሉት ዘንድ መከሩበት፣ ሰይፍ ሳሉለት፣ ጦር አሾሉለት፣ አንገቱን ለግዳይ አዘጋጁት፡፡
ለዓመታት የመከሩበት፣ የዶለቱበትን የሥልጣን ዘመን በሕዝብ ትግል ለቅቀው የእነርሱ ዘመን ተጠናቋል፡፡ ቤተ መንግሥቱን እንደ ቀደመው አይምክሩበትም፣ አይዶልቱበትም፡፡ አድራጊ ፈጣሪነታቸው አቅም አጥቷል፤ አዛዥ ናዛዥነታቸው ኃይሉን ተነጥቋል፡፡ የተሸከማቸው ሕዝብ ከትክሻው አውርዷቸዋል፣ ድንጋይ አንስቶ ከቤተ መንግሥት አስወጥቷቸዋል፡፡ ከቤተ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከቤተ መንግሥት አቅራቢያ ርቀው መደበቂያ ወደአሉት ኮብልለዋል፡፡ ታዳያ የተነጠቁት ዙፋን፣ የራቃቸው ቤተ መንግሥት እንቅልፍ አሳጥቷቸዋል፡፡ ዳግም ወደ ቤተ መንግሥት ለመመለስ፣ ዳግም አድራጊ ፈጣሪነታቸውን የእነርሱ ለማድረግ አብዝተው ዶለቱ፡፡
በትግራይ ተራራዎች እና ሸለቆዎች ሥር ለሥር የበዙ ታጣቂዎችን አሰለጠኑ፡፡ በየአደባባዮቻቸው የታጠቁ ወታደሮችን፣ ለጦርነት የተዘጋጁ ሰልፈኞችን ያሳዩ ጀመር፡፡ ክፉ ሃሳባቸው መጨረሻው የከፋ እንደሚሆን ያዩ ሕዝብ የሚታዘዝላቸው የሃይማኖት አባቶች፣ እርቅ የሚጸናላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንስፍስፍ አንጀት ያላቸው እናቶች ወደ ቀያቸው አምርተው እባካችሁን ጥል ይቅርባችሁ አሏቸው፡፡ ከእግራቸው ሥር ተንበርክከው ተማጸኗቸው፡፡ እነርሱ ግን በተንበረከኩት ላይ ቀለዱባቸው፣ በለመኗቸው ላይ አላገጡባቸው፡፡
አካሄዳቸው ሁሉ አላምር አለ፡፡ ጀንበር ጠልቃ በዘለቀች ቁጥር ማስፈራሪያና ዛቻ ያሰማሉ፣ ማነው የሚነካን እያሉ ይፎክራሉ፡፡ በየቀኑ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተነገረ ጊዜያት ነጎዱ፡፡ እነርሱም ዝግጅታቸውን እንደጨረሱ ባረጋገጡበት ጊዜ የጭካኔ ሰይፋቸውን ዘረጉት፣ በታማኝ አገልጋዩ አንገት ላይ አሳረፉት፡፡
ለሀገርና ለሠንደቅ ክብር ብሎ፣ የሀገርና የሕዝብ አደራ፣ ቃል ኪዳን እና መታመን አዝሎ በምሽግ ውስጥ የሚኖረው ሠራዊት እንደ ወትሮው ሁሉ ጠላት ይመጣበታል ወደላው አቅጣጫ ፊቱን አዙሮ በምሽጉ ከትሟል፡፡ ሀገሩን ጠላት እንዳይደፍራት፣ ወሰኗን እንዳይጥስባት በተጠንቀቅ እየጠበቀ ዓመታትን በምሽግ ውስጥ አሳልፏልና ያን ጊዜም ይህንኑ ነበር ያደረገው፡፡ ጀንበር ብርሃኗን ከልላለች፡፡ ብዙዎች ከድካማቸው ለማረፍ አንቀላፍተዋል፣ ታማኙ ወታደር ግን ዓይኑ እርግብ ሳትል በጨለማው ውስጥ ሊመጣ የሚችል ጠላት ይጠባበቃል፡፡
ጀርባዬ አስተማማኝ ነው ብሏልና በጀርባው አልሰጋም፡፡ ዳሩ የተገመተው ቀርቶ ያልተገመተው ኾነ፡፡ ጀንበር በጠለቀችበት፣ ምድር በጨለማ ካባ በተጠቀለለችበት ምሽት ሊገድሉት ተነስተዋልና፡፡ ያመኑት ከዳቸው፣ የጠበቁት ገደላቸው፡፡ ወያኔ በአሰለጠናቸው ታጣቂዎች ሰይፍ አነሳባቸው፣ በግፍ ገደላቸው፣ ገድሎ አሰቃያቸው፣ መከራውን አጸናባቸው፡፡ ብዙዎች ሲያምኑት በከዳ ወዳጅ ተክድተው ከእነ ቃል ኪዳናቸው አሸለቡ፣ ብዙዎች ልብሳቸውን ተነጥቀው በራቁት ገላ ተንከራተቱ፣ ብዙዎች አካላቸው ጎደለ፡፡ ሀገር የጠበቀውን፣ በደል ያልተገኘበትን፣ ጥፋት ያልተመዘገበበትን ሠራዊት በጎዳናዎች ላይ መኪና ነዱበት፣ የግፍ ግፍ አበዙበት፡፡
ከጀርባው የተከዳው ሠራዊት በእልህ ተነሳ፡፡ የከዱትን ይቀጣቸው፣ የከዱትን ይመታቸው፣ የከዱትን ያንበረክካቸው ዘንድ ተቆጣ፡፡ እንደ አንበሳ የጀገነ፣ እንደ ነብር የፈጠነ ነበርና በኃያል ጀግንነት፣ በአስገራሚ ልበ ሙሉነት የከዱትን ቀጣቸው፣ የወጉትን አደብ አስያዛቸው፡፡ የተከዳው ሠራዊት ጠላቱ ወያኔ እንደሆነ አውቋልና ወያኔን እንደ አመጣጡ መለሰው፡፡ የተከዳው ሠራዊት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከጫፍ ጫፍ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ናቸውና ሕይወት እየገበረ ከአደጋ ከለላቸው፣ እየሞተ አኖራቸው፣ እየደማ አስከበራቸው፣ አጥንት እየከሰከሰ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡
ጥቅምት 24 ልበ ሙለው ሠራዊት የተከዳበት፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሲል በግፍ የሞተበት፣ በግፍ ደምና አጥንት ያፈሰሰበት ነውና ቀኑ አይረሳም፡፡ ኢትዮጵያውያን ለእነርሱ ሲል የሞተላቸውን፣ ለእነርሱ ሲል የተሰቃየላቸውን፣ ለእነርሱ ሲል የተዳፋውን እና የተገፋውን ሠራዊት ያስቡታል፣ ስሙን እያነሱ ይዘክሩታል፣ ለእኔ ነውና የሞትከው እያሉ በልባቸው ያኖሩታል፣ ላይረሱት፣ ላይለዩት ቃል ኪዳን ይሰጡታል፡፡ የከዳውን ወያኔን ደግሞ ያወግዙታል፡፡
አሸባሪው ወያኔ የጠበቀውን የከዳ ቃል ኪዳን አፍራሽ፣ ከሃዲ ነውና ከሀገር ወዳድ ጀግኖች ጋር ኅብረት የለውም፡፡ አዎን ይህችን ቀን ኢትዮጵያውያን አይረሷትም፣ ነገር ግን ጥላቻ አይዘሩባትም፣ ጥላቸው ከሽብር ቡድን ጋር እንጂ ከሕዝብ ጋር አይደለምና፡፡ ጀግኖቹ የተከዱት ለሀገር ፍቅርና ለሕዝብ ክብር ሲሉ ነውና በከበረ ልብ ውስጥ በክብር ይቀመጣሉ፣ በተወደደ ሕዝብ አንደበት ይዘከራሉ፣ በደመቀ የታሪክ መዝገብ፣ ባማረ ቀለም ይሰፍራሉ፡፡
ጀግኖች ኾይ በሞታችሁ ሀገር አኑራችኋልና ክብር ይገባችኋል፣ ጀግኖች ኾይ በአጥንታችሁ ሕዝብ አስከብራችኋልና ምስጋና ይገባችኋል፣ ጀግኖች ኾይ በደማችው ሠንደቅ አጽንታችኋልና ትውልድ ያመሰግናችኋል፡፡ በደም የጻፋችሁት ቃል ኪዳን ይከበራል፣ በከበረ ልብ ውስጥ ይኖራል፡፡ በሞታችሁበት ምድር ጠላት ይጠፋል፣ ፍቅርና ወዳጅነት ይሰፋል፡፡ መልካሙን ሁሉ አድርጋችኋልና በሰላም እረፉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
Previous article“የሰሜን ዕዝ ሰማእታትን በመዘከር ታሪካዊ አደራችንን እንወጣለን” መከላከያ ሠራዊት
Next article“እውነትን ይዞ የታገለ ሁልጊዜ አሸናፊ ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ