“የሰሜን ዕዝ ሰማእታትን በመዘከር ታሪካዊ አደራችንን እንወጣለን” መከላከያ ሠራዊት

171
ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መከላከያ ሠራዊት ጥቅምት 24 የሰሜን ዕዝ ጥቃት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
“የሰሜን ዕዝ ሰማእታትን በመዘከር ታሪካዊ አደራችንን እንወጣለን” ሲል መከላከያ ሠራዊት ገልጿል።
መከላከያ ሠራዊት ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
ኢትዮጵያ በዘመኗ በርካታ ኅልውናዋን የሚጋፉ እብሪት የወጠራቸው ሀገራት ወረራ ፈፅመው ጥቅምና ፍላጎታቸውን ለመጫን ተፈታትነዋታል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጀግና መውለድ ታውቅበታለችና ጀግኖች ልጆቿ ጠላቶቿን በጦርና በጋሻ ተፋልመው እንደአመጣጣቸው በመመለስ ሉዓላዊት ሀገር አስረክበውናል።
አሸባሪው ህወሓት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለ27 ዓመታት እንደፈለገ በሕዝብ ሰብዓዊ መብቶች ላይ ሲረማመድ ቆይቶ ሀገሪቱን ለውድቀት የዳረገ ዘረፋ በማካሔዱና በዚህ ጦስ የነበረውን የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በማጣቱ ገና በለውጡ ጅማሬ የህወሓት አመራሮች ሀገራዊ ለውጡን ማጥላላትን ሥራዬ ብለው ተያያዙት።
የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ መቀመጫውን በትግራይ ክልል አድርጎ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እድሜ ልኩን የኖረ ሠራዊት ነው።
ዕዙ በሰውና በመሣሪያ የመከላከያን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ የተቋሙ ግዙፍ ኃይል ነበር። ወቅቱ መኸር በመሆኑ ሠራዊቱ የአርሶ አደሩን ሰብል መሰብሰብ እና በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በማባረር ውሎ አዳሩን ከትግራይ ገበሬ ጋር አድርጓል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ህወሓት ከሰው ልጅ በማይጠበቅ ጭካኔና በዓለም መድረክ ባልታዬ ክህደት ለዘመናት በቀበሮ ጉድጓድ እየኖረ ሲጠብቀው የኖረውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በተኛበት ጥቃት ከፈተበት።
ሀገር እንጠብቅ ሕዝብ እናገልግል ያሉ፤ ቀን ገበሬ ሌሊት ጥበቃ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ቀን ሀሩሩ ሌሊት ብርዱ ሳይበግራቸው፣ ክረምት ከበጋ የሚለፉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በህወሓት የክህደት በትር ሀገር አማን ብለው በተኙበት ተወጉ።
በዚያ ጥቃት ብዙዎቹ የሰሜን ዕዝ አባላት በግፈኛው የህወሓት ጥቃት ተገደሉ። በቅጡ እንኳ ሳይቀበሩ ጅብና አሞራ በላቸው። በሬሳቸው ላይ ከበሮ እየደለቁ ጨፈሩበት፡፡ ብዙዎቹ እየቆሰሉ አካላቸውን አጡ። እንዲሁም ታፍነው በርሐብና ውኃ ጥም እየተቀጡ ተንገላቱ። እነኝህ ታፋኝ የሰሜን ዕዝ አባላት በግፈኞች ዱላ ተደበደቡ። ተገደሉ። ሴት የሠራዊቱ አባላት በጉልበተኞች ተደፈሩ።
ህወሓት ምንም እንኳ የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ በብሔር እየመረጠ በርካታ ጓዶችን ይግደል እንጂ በወቅቱ “የራሴ” ለሚላቸው የትግራይ ተወላጆች እንኳ ከመጨከን ወደ ኋላ አላለም። የሰሜን ዕዝን በሚያጠቃበት ወቅት ለሴራው ያልተባበሩትን በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አመራሮችንና አባላትን ገድሎ የጭካኔውን ጥግ አሳይቶናል።
የሰሜን ዕዝ አባላት ትምህርት ቤት ሠርተው ሕጻናት ይማሩ ባሉ፣ ጤና ጣቢያ ሠርተው የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት እንቀንስ ባሉ፤ የውኃ ጉድጓድ ቆፍረው እናቶችን ከሸክም በገላገሉ የተከፈላቸው ወሮታ የግፈኛው ህወሓት ጥይት ሆነ።
ህወሓት ከሃያ ዓመታት በላይ ትግራይ ክልል እየኖረ ከአነስተኛ ደመወዙ ቀንሶ ገንዘብ አዋጥቶ፣ እጁና ትክሻው እስኪላጥ ድንጋይ ፈልጦና ተሸክሞ ትምህርት ቤት፣ ጤና ኬላ፣ የወጣቶች መዝናኛ የገነባ፤ የክረምቱን ጭቃ ሳይጠየፍ የአርሶ አደሩን ሰብል ሲኮተኩት እና ሲያርም ከርሞ፤ ጠዋት ብርዱን ቀን ፀሐዩን ሳይፈራ የደረሰውን ሰብል ሲያጭድ እና ሲወቃ፤ ምሽግ ውስጥ እየኖረ የጠበቀውን፣ የሞተለትንና የቆሰለለትን የሰሜን ዕዝ ሠራዊትን ክዶ የወጋ የጭካኔና የክህደት ጥግ መታወቂያው የሆነ የማፍያዎች ጥርቅም ነው።
አሸባሪው ህወሓት የጥቅምት 24ቱ የሰሜን ዕዝ የክህደት ጥቃት አልበቃው ብሎ ለሌላ ጦርነት ከመሰለፍ ወደኋላ አላለም። በ2013 ዓ.ም ሰኔ ወር መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሠራዊቱን ከትግራይ ባስወጣበት ወቅት በየበርሃው ተበታትኖ የነበረውን ታጣቂውን አሰባስቦ የአፋርና አማራ ክልሎችን በስፋት ወረረ። በዚህ ወረራ ወቅትም አመራሮቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ መሔድ ካለባቸው እንደሚሔዱ እየማሉ ተናገሩ።
በአማራና አፋር ክልሎች ምንም የማያውቁ ንጹሐን ላይ ከባድ መሣሪያ በመተኮስ እና በጅምላ በመረሸን የጥፋት መሐላቸውን በተግባር አሳዩን። ጭና፣ ጋሊኮማ፣ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ያለርህራሔ ንጹሐን ዜጎችን በጅምላ ገደሉ።
ከትልልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ ገበሬው ቤት ድረስ ዘረፉ፣ አወደሙ፣ አቃጠሉ። የአርሶ አደሩን ሰብል አጭደውና ወቅተው ከመውሰድ እስከ እሳት ማቃጠል የደረሰ ጉዳት አደረሱ። ህሊናቸውን የሸጡ ህወሓታዊያን ከመነኩሴ እስከ ሕጻናት ያሉ ሴቶችን አስገድደው ደፈሩ።
የጀመሩት ወረራ በጀግናው ሠራዊታችን ጠንካራ ምት ተፈረካክሶ ከአፋርና አማራ ክልል ተጠራርገው ሲወጡ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ ባለበት ሰዓት ነሐሴ 18 ቀን ሦስተኛ ወረራ ከፈቱ።
ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት መሔድ ከነበረባቸው ሕጻናት እስከ መነኩሴ ድረስ በግድ ወደ ግንባር በማምጣት የትግራይን ሕዝብ ለጥይት ማብረጃነት ተጠቀሙበት፡፡
ህወሓት ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች እስከ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ወረራ ቢከፍትም የብርቱውን ሠራዊታችንን ክንድ መቋቋም አልቻለም። ትንሽ ድል ሲያገኝ የሚፎክረው፤ ሲሸነፍ ደግሞ የሚያለቅሰው ህወሓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፈው ከፍተኛ ሀብት የውጭ ሀገር ሰዎችን (ሎቢስት) ቀጥሮ ፕሮፖጋንዳ ቢያስነዛም ውጤቱ ኪሳራ ሆኖበታል።
ይህን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮውን ለማሳካትም አንዴ በጦርነት ሌላ ጊዜ ደግሞ በድርድር ጊዜ ሸምቶ ለማገገም ያለመታከት እየሠራ ይገኛል። ግን እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን። በየትኛውም ግንባር እንፈተናለን እንጂ ፈፅሞ አንሸነፍም።
ምንም እንኳ አሸባሪው ህወሓት ቀደም ብሎ በሰሜን ዕዝ ላይ ቀጥሎም በመላው ኢትዮጵያ ላይ የፈፀመው ጥቃትና ወረራ መዘዙ እስከዛሬ ድረስ ዘልቆ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጫና ያስከተለ ቢሆንም ሁሉንም በአሸናፊነትና ድል እየተወጣን እንገኛለን።
ከመላው ሕዝባችን ጋር ሆነን ባደረግነው ታላቅ ተጋድሎ ህወሓት ራሱ በለኮሰው ጦርነት ሊጠፋ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡
የሰማዕታቱን ፍሬ የምናይበትና ድሉን የምንዘክርበት ወቅት ላይ ነን።
እኛ አደራ የምንዘነጋ ሳንሆን የወንድሞቻችንን፣ የኢትዮጵያን ክብርና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ተጋድሎ ከዳር ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት በጀግንነት ለመክፈል የተዘጋጀን ነን።
አሸባሪው ህወሓት የፈፀመብን በደልና ሰቆቃ ተቆጥሮ የማያልቅ በታሪክና ትውልድ ፊት ይቅርታ የማይቸረው ነው፡፡ በወንድሞቻችን ላይ የደረሰውን ግፍና መከራም መቼም አንረሳውም፡፡ ነገር ግን እኛ እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኃይል ሕዝብና ሀገርን አፅንተን የምናስቀጥል ሕዝባዊ ሠራዊት ነን፡፡
ስለሆነም በደልን ስንቆጥር የምንኖር ሳንሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ከህወሓት የዘመናት ባርነትና ጭቆና ነጻ ለማውጣት የከፈልነውንና እየከፈልን ያለነውን መስዋእትነት አጠናክረን በመቀጠል የመጨረሻው የድል ዋዜማ ላይ ሆነን ሰማእታትን እየዘከርን ኢትዮጵያችንን አስከብረን በአሸባሪው ህወሓት መቃብር ላይ ድላችንን እናበስራለን።
“ጥቅምት 24 መቼም አንረሳውም!!”
ክብርና ሞገስ ለተሰው ሰማእታት!!
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
Previous articleʺየተዋበው ንጉሥ፣ በተዋበው ዙፋን”
Next articleʺያመኑት ከዳቸው፣ የጠበቁት ገደላቸው”