
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግና የጦር መሪ ወለዳቸው፣ ጀግናው በእቅፉ ውስጥ አሳደጋቸው፣ የጀግንነት ሥራ አሳያቸው፣ ከጀጎኖች ጎራ ከጀግኖች ጋራ አሳደጋቸው፣ የሀገር ፍቅር አስተማራቸው፣ ለክብርና ለሠንደቅ መሞትን ቀረጸላቸው፡፡ ሀገር ከሕይወት ትበልጣለች፣ ሠንደቅ ከደምና አጥንት ትልቃለች እያለ አስተማራቸው፡፡ የማይሻር ቃል ኪዳን አስረከባቸው፡፡
የደም ግብዓታቸውን ያየ ሁሉ ያደንቃቸዋል፣ ከዙፋናቸው ግርጌ ኾኖ በአግራሞት ይመለከታቸዋል፣ ነገሥታቱ ከወገባቸው ጎንበስ፣ ከአንገታቸው ቀለስ እያሉ እጅ ነስተዋቸዋል፣ በየደረሱበት ሁሉ በአልማዝ ባጌጠ መረማመጃ አራምደዋቸዋል፣ ባማረ ቤተ መንግሥት፣ በረቀቀ መቀመጫ አስቀምጠዋቸዋል፡፡ ለክብራቸው ይኾን ዘንድ ከወርቅ የተሠራ ሰይፍ አስጨብጠዋቸዋል፣ በአልባዝ ያጌጠ ዘውድ ጭነውላቸዋል፣ በወርቅና በአልማዝ የተንቆጠቆጠ ካባ ደርበውላቸዋል፣ እጹብ የሚያሰኝ በትረ መንግሥት አስይዘዋቸዋል፡፡

ወይዛዝርቱ በእልልታ ይቀበሏቸዋል፣ ጎበዛዝቱ በሆታ ያከብሯቸዋል፣ የዓለም አጫዋቾች ያመረውን ስንኝ ይደረድሩላቸዋል፣ ለክብራቸው የሚመጥነውን ግጥም ይገጥሙላቸዋል፣ ስማቸውን እያነሱ ያወድሷቸዋል፡፡
የጦር አበጋዞች ይወዷቸዋል፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ ይሳሱላቸዋል፣ አበው ያከብሯቸዋል፣ መንገዳቸው የሰመረ፣ ስማቸው የከበረ፣ ግርማቸው የታፈረ ይሆን ዘንድ ይጸልዩላቸዋል፡፡ አስፈሪ ግርማ ያለው ሠራዊት በፊት በኋላቸው፣ በቀኝ በግራቸው ያጅባቸዋል፣ የበዛ ሕዝብ ይከተላቸዋል፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ አምረውና ተውበው ይከቧቸዋል፣ አስፈሪ ግርማ ያላቸው የጦር አበጋዞች ይጠብቋቸዋል፡፡
ከአባት ቃል ኪዳን የተቀበሉት፣ በጀግና እቅፍ ያደጉት፣ ከጀግኖች ጋር የኖሩት ታላቁ ሰውም የሚወዳቸውን ሕዝብ ይወዱታል፣ የሚያከብራቸውን ሕዝብ ያከብሩታል፣ ከመውደዳቸው የተነሳ አብዝተው ይሳሱለታል፡፡ በክብርና በፍቅር ይኖር ዘንድ ይተጉለታል፡፡
ታላቁ ንጉሥ አጼ ምኒልክ ዘመናቸው እንደተጠናቀቀ አውቀዋልና፣ አልጋቸውን የሚወርስ፣ ካባቸውን የሚለብስ፣ በቀየሱት መንገድ የሚመላለስ ወራሽ ፈለጉ፡፡ አውጥተው አወረዱ፡፡ በዘመኑ የእርሳቸውን አልጋ የሚወርስ ከብላቴናው ልጅ ኢያሱ በስተቀር ሌላ ሰው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ዙፋናቸውን ከታላቅ ቃል ኪዳን እና ከከበረ የሀገር ፍቅር ጋር ለልጅ ኢያሱ አወረሱ፡፡ ብላቴናው ልጅ ኢያሱም ታላቁን አደራ ተቀበሉ፡፡
ልጅ ኢያሱም የተሰጣቸውን ቃል ኪዳን ይፈጽሙ ዘንድ ታተሩ ፡፡ ዳሩ ረዘም ላለ ዘመን በዙፋኑ ላይ መቀመጥ አልቻሉም፡፡ ንግሥናው የምኒልክ ልጅ፣ የኢያሱ እናት እህት ልዕልቷ ዘውዲቱ ተቀበሉ፡፡ በዛም ጊዜ የምኒልክ ታማኝ የጦር አበጋዝ እና የቅርብ ዘመድ የነበሩት የራስ መኮንን ልጅ መልከ መልካሙ ተፈሪ አልጋ ወራሽ ኾነው ተሾሙ፡፡ ገና በለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ከቤተ መንግሥቱ አሠራር ጋር የተዋወቁት ተፈሪ መኮንን ለአልጋ ወራሽነቱ የተገቡ ሰው ናቸው ተባለ፡፡

ዘመን ዘመን እየገፋ መጣ፡፡ የቤተ መንግሥት ስርዓቱ እየተለዋወጠ ሄደ፡፡ ተፈሪ መኮንንም አልጋ ወራሽነትን እና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴነትን ሳይለቁ የንጉሥነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ ከእሳቸው በላይ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ አሉ፡፡ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ የንግሥና ማዕረጉን ለተፈሪ መኮንን በሰጡ ጊዜም ʺ እግዚአብሔር እኔን መርጦ በአባቴ በዳግማዊ ምኒልክ አልጋ ሲያስቀምጠኝ አንተንም ለእኔ አጋዥና ረዳት እንድትሆነኝ አድርጎ መርጦሃልና ስለዚህ ከእኔ በታች ንጉሥ አድርጌ እነሆ ለክብርህ ዘውድ ሰጠውህ፡፡ ወደፊትም ለንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ ወራሽ ለመሆን ያብቃህ፡፡ በምትሠራውም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ይርዳህ” አሏቸው፡፡
ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ለተፈሪ መኮንን የንግሥና ማዕረግ ከሰጡ በኋለ ረጅም ዘመን አልቆዩም፡፡ ከእነ ክብራቸው ወደ ማይቀርበት ዓለም አሸለቡ፡፡ አስቀድመው ለንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ ያብቃህ ብለው መርቀዋቸው ነበርና የንጉሠ ነገሥቱን ዘውድ የሚጭኑበት ዘመን መጣ፡፡ ተፈሪ መኮንን አባ ዳኛው ምኒልክ፣ እነ ልጅ ኢያሱ እና እነ እቴጌ ዘውዲቱ በተቀመጡበት ዙፋን ሊቀመጡ ቀኑ ደረሰ፡፡
ወረኃ ጥቅምት ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ለወረኃ ኅዳር የጊዜ ቀመሩን ሊያስረክብም የተቃረበ መስሏል፡፡ መንግሥታት ወደ ተቀደሰችው ምድር ኢትዮጵያ ይመጡ ዘንድ ታላቅ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፣ ጥሪውን ተቀበሉ፡፡ ብዙዎች ተወካዮቻቸውን ወደ አዲስ አበባ ላኩ፡፡ አዲስ አበባ ታላቅ ድግሥ ደግሣለች፣ ቤተ መንግሥቱ ተውቧል፣ ጎዳናዎቿ አምረዋል፡፡ ነጫጭ ፈረሶች ባጌጠ ልብስ ተውበው ይመላለሳሉ፣ የጦር አበጋዞች፣ ሊቃውንት ወደ ከተማዋ ይጎርፋሉ፡፡
ልብሰ መንግሥቱ፣ ዘውዱና ሉሉ፣ በትረመንግሥቱ፣ ሰይፉ፣ የተዋበው ቀለበቱ፣ ያማረው ነገር ሁሉ በወርቅና በአልማዝ አሸብርቆ ተሠራ፡፡ ለአልጋ ወራሾችና ለመሳፍንቱ ከሚሠራው የራስወርቅ የበለጠ ለእርሳቸው ተሠራ፡፡ የአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው ተጠናቅቆ በኢትዮጵያ ምድር ኃያሉን ስልጣን ሊይዙት፣ ከኃያሉ ዙፋን ላይ ሊቀመጡበት ነውና፡፡ ለመኳንንቱና ለመሳፍንቱ ሚስቶች፣ ለወይዛዝርቱ እንደየማዕረጋቸው ጌራወርቅ ተሠራላቸው፡፡ ለጦር አለቆችም የአንበሳ ጋማ ፀጉር ከወርቅ ጋር እየተሰባጠረ በከፋይ የተለጠፈ ልብስና ቆብ ተሰፋላቸው፡፡
ቀኑ ደረሰ፡፡ ዕለተ ቅዳሜ ለዕለተ እሁድ ስልጣኑን አሳልፎ ሊሰጥ መሸጋገሪያው ሌሊት በምድር ላይ ዙፋኑን ጥሏል፡፡ ጨለማ በምድር ነግሷል፡፡ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጸድ ሥር ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን እና አንባቢያን ተሰባስበዋል፡፡ ሊቃውንቱ በጸጋው በልብሰ ተክህኖ አጊጠዋል፣ ያያቸው ሁሉ ነብሱ ሀሴትን ታደርጋለች፡፡ በዕለተ ሰንበት ከተከበረችው ቀን በተጨማሪ ታላቅ በዓል አለና ሁሉም አምሮ ተውቧል፡፡

ካህናቱ ማሕሌቱን ጀምረውታል፡፡ መውደሱ፣ ክስተት አርያም እየተባለ ነው፡፡ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተመቅደስ ምድራዊ የማይመስል የካህናት ኅብረ ዝማሬ ይታያል፣ ያን የተወደደ እና ያመረ ምስጋና አይቶ ማን ምድራዊ ነው ይላል፣ ይሄስ በምድር የሆነ፣ ከምድርም የተለየ እጽብ ደንቅ ነው ይላል እንጂ፡፡
ጥቅምት 22 ለጥቅምት 23 ቅደሜ ለእሁድ አጥቢያ እኩለ ሌሊት ገደማ ለታላቁ ዘውድ የታጩት፣ ለቅብዓ ሜሮን የተዘጋጁት፣ ለዙፋን የሚጠበቁት፣ በትረ መንግሥቱን የሚጨብጡት ንጉሥ በተዋበ ደም ግብዓታቸው ላይ አሥሪ የንግሥና ልብስ ለብሰው፣ እንደ እርሳቸው ሁሉ ያማረ ካባ የደረቡትን ባለቤታቸውን አስከትለው፣ በበዙ መኳንንት፣ መሳፍንትና የጦር አለቆች ታጅበረው ወደ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አቀኑ፡፡ የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል በሚከብርበት በዕለተ ጊዮርጊስ፣ በመናገሻ ጊዮርጊስ አጸድ ሥር ሌላ በዓል አለና ዋዜማው ደምቋል፡፡
በአጸዱ ዙሪያ በደረሱ ጊዜ ለዙፋን ለመረጣቸው አምላክ ምስጋና አቀረቡ፡፡ በምድር እጅ የሚነሳላቸው ንጉሥ ለሁሉም ገዢ ለፈጣሪ ሰገዱ፣ እጅ ነሱ፣ በረከትና ረድኤት ይሰጣቸው፣ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን ይጠብቅላቸው፣ ብርታትና ብልሃት ይሰጣቸው ዘንድ ተማጸኑ፡፡ አበው ሊቃውንት የተወደደችውን፣ የተመረጠችውን፣ በታሪክም ከፍ ከፍ ያለችውን ኢትዮጵያ ሀገራቸውን በትጋት ይመሩ ዘንድ መረቋቸው፣ ንጉሡን ከዙፋኑ አያሳጣን አሉ፡፡ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ መቅደስ የተሰባሰቡ ካህናት ያለ ድካም ስርዓቱን ሲያደርሱ አደሩ፡፡ ሌሊቱም ነጋ፡፡

መሳፍንትና መኳንንት ሙሉ የማዕረግ ልብሳቸውን ከኒሻን ጋር ለብሰው የራስ ሉልና የራስ ወርቅ ደፍተው በአዳራሹ ውስጥ በተሰናዳላቸው ስፍራ በየማዕረጋቸው ተቀመጡ። የውጭ ሀገር መንግሥታት መልእክተኞችም ሙሉ የማዕረግ ልብሳቸውን ለብሰው በተሰናዳላቸው የክብር ስፍራ ተቀመጡ። ጳጳሳትና መምህራን በመንበሩ አጠገብ በወለሉ ላይ ቆመው ለሚቀጥለው ሥርዓት ተዘጋጁ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ለቅብዓ ሜሮን በተዘጋጀላቸው ሥፍራ ኾኑ፡፡
ጊዜው ደርሷል፡፡ አሥፈሪው ዘውድ፣ በመልከ መልካሙ ንጉሥ ራስ ላይ ሊደፋ ነው፡፡ አቡነ ቄርሎስ ወንጌል ዘወርቁን ለንጉሡ አስጨበጧቸው፡፡ ቃለ መሃላም አስፈጸሟቸው፡፡ በጳጳሳቱ አማካኝነት ስርዓተ ጸሎት ተደርጎ ቅብዓ ሜሮን ተቀቡ፡፡ ንጉሠ ነገሥት ተሰኝተው ዘውድም ተጫነላቸው፡፡ የአልማዙንም ቀለበት አደረጉላቸው፡፡ እቴጌ መነንም እንደ ግርማዊነታቸው ሁሉ ተደረገላቸው፡፡ ይህም የሚሆነው ያለ ምክንያት አይልነበረም፣ ሁሉም በምክንያትና በጠበቀ ስርዓት ይፈጸም ነበር እንጂ፡፡ እልልታው ደመቀ፤ ምድር በደስታ የተናወጸች መሰለች፣ መለከት ተነፋ፣ እንቢልታው ጮኸ፣ ከበሮው ተመታ፣ እጆች አጨበጨቡ፣ እግሮች አሸበሸቡ፣ አንደበቶች ሁሉ እልል አሉ፡፡ ለምን የተዋቡት ንጉሥ፣ በተዋበው ዙፋን ላይ ተቀምጠዋልና፡፡
ንጉሡ ስርዓተ ንግሥናቸው ሲፈጸም በዙፋናቸው ላይ ተቀመጡ፡፡ ያን ጊዜ መሳፍንትና መኳንንትም የራስ ሉላቸውንና የራስ ወርቃቸውን ከየራሳቸው እያወረዱ በንጉሠ ነገሥቱ ፊት እያጎነበሱ እጅ ነሡ። የቤተ መቅደሱም ሥርዓት ተፈጸመ፡፡ ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፤ ዘውዳቸውን ጭነው፤ በትረ መንግሥታቸውን ይዘው፤ ሉል ጨብጠው ከቤተ መቅደስ ወጡ። ሕዝቡ የሰሌን ቅጠል በእጁ ይዞ ጎዘጎዘላቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱና እቴጌይቱ በስድስት ፈረሶች በሚሳብ በወርቅ ሠረገላ ተቀመጡ፡፡ ከፊትም ከኋላም በመሳፍንትና በመኳንንት ታጅበው በወታደርና በሠራዊት ሰልፍ መካከል አልፈው ወደ ቤተ መንግሥታቸው ተመለሱ። መሳፍንትና መኳንንት የመንግሥታት መልእክተኞችም በየማዕረጋቸው በሠረገላ ሆነው አጀቡ። እምቢልታውና መለከቱ ተንካለለ፤ ነጋሪቱ እየተጎሰመ ገብር ገብር ሲል እጹብ ድንቅ ተባለ፡፡ ሕዝቡ ሺህ ዓመት ይንገሡ አላቸው፡፡ በዚች ቀንም ታላቅ ግብር በቤተ መንግሥት ተደረገ፡፡
የንግሥና በዓሉም ያማረ ኾነ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ኾነው ቅብዓ ሜሮን የተቀቡባት የዘውድ በዓላቸው የተፈጸመባት ጥቅምት 23/1923ዓ.ም ነበር፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!