
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የጥቅምት 24 ጥቃትን ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ጥቅምት ሃያ አራት አሸባሪው እና ጡት ነካሹ ወያኔ ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ለመፈጸም በጀግናው ሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የፈጸመበት ዕለት በመሆኑ በታሪክ ሲታሰብ ይኖራል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ የተወጋችበት፣ ጥቁር ማቅ የለበሰችበት ዕለት ነው። አሸባሪው ወያኔ እኔ ያልዘወርኳት ሀገር ትፍረስ በሚል የሆዳምነት እሳቤው በርካታ ተግባራትን ሲያደርግ የቆዬ ቢሆንም በጀግና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ በመጣል ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ይፋ አድርጓል።
ድርጊቱ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ክፍለ ዓለማት ያልተሰማ፣ ያልተፈፀመ የጭካኔ ልኬት የማይገኝለት ተግባር ነው። ዕለቱን ትውልድ ሊያውቀው እና ዳግም እንዲህ ዓይነት ወንጀል በሀገሪቱ እንዳይደገም በታሪክ ሲዘከር ይኖራል።
ዕለቱ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በልዩ ዝግጅት የሚከበር ሲሆን በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድም ታስቦ ይውላል።
በሠራዊቱ ላይ የተፈፀመው የጭካኔ ድርጊት ትምሕርት ሆኖ ከብሔርና ፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ጠንካራና አስተማማኝ መከላከያ እንዲገነባ አድርጓል።
አሸባሪው ወያኔ የጭካኔ ድርጊቱን የፈፀመው ከብሔር እና ፖለቲካ የፀዳ ስላልነበር ነው።
የጥቅም ት 24/2013 ዓ.ም ድርጊት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስቆጣ በመሆኑ ሕዝቡ ከመከላከያ ግን ተሰልፎ ሀገሩን አስቀጥሏል፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
