የቤተ እምነት እና የምዕመኖቿን ደኅንነት ለመጠበቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ቤተ ክርስቲያኗ አስታወቀች፡፡

238

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በየስድስት ወሩ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ በተላለፈ መልዕክት እንደተገለጸው የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያን እና በምዕመናኑ ላይ በሚደርሰው ተፅዕኖ ከቀያቸው የተፈናቀሉት ወገኖች በርካታ ናቸው፤ ስጋቱ አሁንም አለ፡፡ አለመረጋጋቱ እንዳይቀጥል ለማድረግ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባም ነው የተነገረው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳ ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘ መንበረ ተክለሃ ይማኖት አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የቤተ ክርስቲያን መብት እና ክብር ሊያስጠብቅ እና ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን ለህግ ሊያቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡

“ከእንግዲህ በኋላ በብልሹ አሠራር የሚተራመስ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ሊኖር አይገባም፤ በዚህ ዓመት አሠራሮቻችን ሁሉ አስተካክለን ወደ ምዕመናን ጥበቃ እና ልማት ስራዎቻችን እንሸጋገራለን” ብለዋል አቡነ ማትያስ፡፡

ከውጭ ሆኖ በገንዘብ፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ እርስ በርሳችን የሚከፋፍልን ሃይል ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ያለውን ያልዘመነና የምዕመናንን ልቡና እያቆሰለ የሚገኝን የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አሠራር ችግር ከስረ መሠረቱ ማስተካከል ካልቻልን ችግራችን ሊቀረፍ አይችልም ነው ያሉት ፓትሪያርኩ፡፡

የቤተ ክርስቲያኗን ዙሪያ መለስ ጥቃት እና ችግር ለመከላከል ብሎም ለማስቆም የሚያስችል እና በየአካባቢው ያሉ ጥቃቶችን፣ ወከባዎችን እና አድሏዊ አሠራሮችን እየተከታተለ ትክክለኛ መረጃ ለምዕመኑ የሚያደርስ የመረጃ ግብረ ሃይል በጉባኤው ይቋቋማልም ተብሏል፡፡

ጉባኤው ዛሬ ከፓትሪያርኩ የመክፈቻ ንግግር በኋላ በዝግ ተጀምሯል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው – ከአዲስ አበባ

Previous articleጅጌ- የምንጃሮች ኅብረት መገለጫ!
Next articleየጸጥታ ችግሩን ተከትሎ መንገድ ተዘግቷል፤ መንገደኞችም ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡