
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አፍሪካ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አይቀሬ መሆኑን ገለልጸዋል።
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ እውን የሚያደርጉ በርካታ ዕድሎች አሏት ብለዋል።
እ.አ.አ በ2030 መጨረሻ ላይ ዓለም ከሚኖራት ወጣት ትውልድ ውስጥ 40 በመቶው የአፍሪካ ወጣቶች እንደሚሆኑ ገልጸው፤ ቀጣዩ የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ መሪ የምትሆኑት ዛሬ በመካከላችን የምትገኙት እናንት ወጣቶች ናችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
21ኛው ክፍለ ዘመን ከገባ ጀምሮ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ባለው መንገድ እየጨመረ መሆኑን እና አህጉሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዕድገት እየገሰገሰች መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲስ የሥራ ፈጠራዎች እና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በአፍሪካ ምድር እያበቡ መሆኑ ለአህጉሪቱ ዕድገት ምክንያት መሆናቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተናገሩት።

በአፍሪካ አህጉር በቀል የሆኑ ቴክኖሎጂዎች በአህጉሪቱ ከመስፋፋት አልፈው ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች እየተሻገሩ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ሀገር በቀል እና አህጉር በቀል ቴክኖሎጂዎች አህጉሪቱ የሚያጋጥሟትን መጠነ-ሰፊ ፈተናዎች ለመሻገር የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካ 4ኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት መጀመሯን ጠቅሰው፣ በቅርቡ በተካሄደው የፓን አፍሪካን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ፎረም ላይ እያደጉ የመጡትን ቴክኖሎጂዎችን አቅም በማጠናከር ዘላቂ ልማት ማምጣት የሚቻልባቸው ስትራቴጂዎች መቀረፃቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካ የተያያዘችውን የዕደገት ጉዞ ለማስቀጠል የኢኮኖሚያችንን መዋቅራዊ ትራንፎርሜሽን እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።
ይህም ምርትን ማስፋፋት፣ ንግድን እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዲሁም ኢንዱስትሪን በማፋጠን የጥሬ ዕቃ አምራችነት ሚናችንን እሴት ጨምረን ወደ መላክ መቀየር መሆኑን ጠቁመዋል፤ ይህንን ማድረጉ የበለጸገ ሕዝብ የሚፈጥር ሂደት መሆኑን ነው የገለጹት።
የአፍሪካ ሀብት የተትረፈረፈ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ዓለም ካሏት ታዳሽ እና ታዳሽ ካልሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ውስጥ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ በአህጉሪቱ የሚገኙ እንደሆነ ጠቁመዋል። ዘገባው የኢብኮ ነው።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
