
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት ለከተማዋ የሚያገለግል መዋቅራዊ ፕላን በማዘጋጀት ለከተማ አሥተዳደሩ አስረክቧል።
መዋቅራዊ ፕላኑ በታቀደው ልክ ተግባራዊ ከተደረገ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ፣ ተወዳዳሪ፣ ዓለማቀፋዊ ሁነቶችን ለማዘጋጀት የምትመችና ለቱሪዝም ተመርጣ የምትጎበኝ ከተማ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
መዋቅራዊ ፕላኑ ከሕጋዊነት እስከ መሰረተልማት ግንባታና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እንደኾነ ነው የተነገረው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን ተጠናቆ ወደ ተግባር ከተገባ አንድ ዓመትን አስቆጥሯል።
እስካሁን ባለው ሂደት በተግባር ምዕራፉ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች እና ሊስተካከሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መዋቅራዊ ፕላኑን ያዘጋጀው የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር፣ የከተመዋ ነዋሪዎች እና ሌሎች ተገባዥ አካላት በተገኙበት ምክክር ተካሂዷል።
አቶ ዋሴ ተፈራ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የፕላን ዝግጅት እና ክትትል ቡድን መሪ ናቸው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን ተጠናቆ ወደ ተግባር ከተገባ አንድ ዓመትን እንዳስቆጠረ ነው የተናገሩት።
እስከ አሁን ባለው የተግባር ሂደት አዲሱ የቤት ማኅበራት የመኖሪያ ቤት ምሪት አዲሱን የከተመዋ መዋቅራዊ ፕላን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።
በመዋቅራዊ ፕላኑ መሰረት ሰፋፊ መንገዶች፣ የአረንጓዴ ልማት ቦታዎች፣ የንግድ ቦታዎች እና ሌሎችም በአዲሱ መዋቅራዊ ፕላን ለማስፈጸም ተሞክሯል ነው ያሉት።
አቶ ዋሴ ለአሚኮ እንደተናገሩት መዋቅራዊ ፕላኑን በሚገባ ሊያስፈጽም የሚችል የተደራጀ አሠራር እና የበጀት ችግር እንዳጋጠመ ነው የተናገሩት። ከሰው ኃይል እስከ መዋቅራዊ ፕላን በታቀደለት ጊዜ ለማስፈጸም ፈተና ሁነዋል ብለዋል።
በከተመዋ በቀደመው የተቀናጀ ፕላን የተሰሩት ቤቶችና ሌሎችም በሂደት የሚፈቱ ይኾናል ያሉት አቶ ዋሴ የወቅቱ ትኩረት አዳዲስ የቤት ግንባታዎች፣ መሰረተልማቶች ሌሎችም ግንባታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
የታቀደውን የከተማ ልማት እውን ለማድረግና የምንመኛትን ከተማ ለመገንባት ከማሕበረሰቡ እስከ አስፈጻሚው አካል ቅንጃታዊ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኒቨርስቲዉ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ.ር) ተናግረዋል። ከተመዋን “ዉቢቷ ባሕር ዳር” የምንላት ተፈጥሮ አድሏት እንጂ ሰርተንባት፣ አልምተናት ነው ለማለት እንቸገራለን ያሉት ዶክተር ፍሬው ተገኝ ይህ መዋቅራዊ ፕላን በተግባር ተገልጾ የምንመኛት ከተማ እንድትኾን ትብብራችን ይቀጥላል ነው ያሉት።
አንድን ከተማ ከዘፈቀዳዊነት የወጣ ጽዱ፣ ውብ፣ ሁሉን አቀፍ መዋቅራዊ አሠራር፣ ለአገልግሎት ምቹ እንዲኾን ለማድረግ የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ያስፈልጋል ለዚህ ደግሞ ሕብረተሰቡን ጨምሮ የሚመለከተው ሁሉ
ለባሕር ዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ተፈጻሚነት ተባባሪ መኾን ይገበዋል ብለዋል።
“የባሕር ዳር ከተማን መዋቅራዊ ፕላን በማስጠበቅ ከተማዋን ውብና ለነዋሪዎቿ የምትመች ለማድረግ እንሠራለን” ያሉት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።
የባሕርዳር ዩኒቨርስቲ የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን በማዘጋጀት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የእውቀት ማዕከል እንደመኾኑ መጠን ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በሌሎች ጉዳዮችም በጋራ እየሠሩ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ዩኒቨርስቲው ከዚህም በተጨማሪ በመሬት ልማት ጉዳዮች ላይ ለከተመዋ ያደረገው አበርክቶ የሚበረታታ እና በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
ለከተማዋ እቆረቆራለሁ የሚለው ብዙ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ ነገር ግን ወደ ተግባር ምዕራፍ ሲገባ ለከተማዋ ፕላን መተግር ሁላችን በኃላፊነት ልንሠራ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለመዋቅራዊ ፕላኑ መሳካት ተባባሪ መኾናቸውን ደግሞ በምክክር መድረኩ የተገኙ የከተመዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!