ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ግብሩ ገድል መለያውም ድል ነው!

180
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊነት ወደቁ ሲባል መነሳት፤ አበቃላቸው ሲባል ማንሰራራት ነው። ኢትዮጵያዊነት ጠፉ ሲባል መብዛት፤ ተሰበሩ ሲባል መበርታት ነው። ኢትዮጵያዊነት ከግለሰብ ፍላጎት በላይ ለሀገር፤ ከግል ጥቅም በላይ ለወገን ጥብቅና መቆም ነው። ኢትዮጵያዊነት በፍትህ ማመን በራስ መተማመን ነው። ኢትዮጵያዊነት በጨለማ ጊዜ መጽናት፣ በፈተና ወቅት መበርታት እና በትግል ዓለም ገድል መሥራት ነው።
ኢትዮጵያም፣ ኢትዮጵያዊነትም ፈተና ላይ የወደቁበት ኅልውናቸው ያከተመበት የሚመስሉ የፈተና ጊዜያቶች ደግመው ደጋግመው ተከስተዋል። ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ መድኃኒት አልባ ህመም የገጠማት፤ ተስፋ አልባ ፈተና ያመሰቃቀላት መስላ ታይታለች፡፡ ስለኢትዮጵያ ክፉዎች ኃይል አግኝተው ብርቱዎች የተሸነፉ የመሰሉበት ወቅት አጋጥሟል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጠላቶቿ ደስታ ተጎናጽፈው አጋሮቿ አንገት ደፍተው የታዩበት የጨለማ ወቅትም ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የመከራ ጊዜያት ትናንሽ የተስፋ ጭላንጭሎችን የሚያያቸው፤ ጥቃቅን ብርቱ የአሸናፊነት ድምጾችን የሚሰማቸው ያጡበትን አግላይ ዓለም አቀፍ የፍትህ አደባባዮችን አስተናግዳለች፡፡ በእነዚያ የፈተና ጊዜያት ሁሉም ኢትዮጵያን የከበባትን ጨለማ እንጂ በርቀት የሚስተዋለውን የተስፋዋን ብርሃን አላዩም፡፡ ብዙዎች በኢትዮጵያ ውድቀት መታበይን እንጂ ለፍትህ ጥብቅና መቆምን አልመረጡም ነበር።
ኢትዮጵያ የራሷን ነጻነት አጥብቃ የመፈለጓን ያክል የሌሎችን ነጻነት እና ክብርም አብዝታ ታከብራለች። በፍትህ እና ፍትሃዊነት እምነቷ የጠነከረው ኢትዮጵያ ለጭቁኖች መብት ለተገፉት ነጻነት ብርቱ አጋር ናት። ኢትዮጵያ በሽምግልና የምታምን በገለልተኛ አቋም የማታወላውል ዲፕሎማት ናት። ኢትዮጵያ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ገለልተኛ መሆን ካለባት ገለልተኛ ትሆናለች፤ ዓለም ጎራ ሲለይ ኢትዮጵያ ደግማ ደጋግማ ገለልተኛ አቋም አራምዳ የዓለምን ሚዛን የሳተ የዲፕሎማሲ መስመር ትዝብት ላይ ጥላለች።
በዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ከተከሰቱ ዓለም አቀፋዊ የታሪክ እውነታዎች መካከል ሊጠቀስ የሚገባው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ የምዕራብ አውሮፓ የክርስቲያኑ ዓለም እና በአፍሮ ኤዥያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የኢስላሙ ዓለም መካከል ዓለም አቀፋዊ የበላይነት ለመያዝ ከ1095 እስከ 1365 ዓ.ም ድረስ ለ300 ዓመታት ያክል የመስቀል ጦርነት ሲካሄድ ኢትዮጵያ የነበራት ገለልተኛ አቋም ነው።
የኢትዮጵያ የዘመናት የዲፕሎማሲ መስመር ጥሎ ማለፍ ላይ የቆመ ሳይሆን ተደጋግፎ መዝለቅ ላይ የተመሰረተ ነው። የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መስመር ዘርፎ ማደግ ሳይሆን ተደጋግፎ መበልጸግን ያለመ ነበር። ኢትዮጵያ እንደ ዛሬው የባሕር በር አልባ ሀገር ከመሆኗ በፊት የባሕር በሮቿ ጦር የሚሰበቅባቸው ሳይሆኑ ንግድ የሚጧጧፍባቸው የትብብር እና አብሮ የመኖር ቅን እና ክፍት በሮች ነበሩ። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ግብሩ ገድል፤ መለያውም ድል ነው!
አንድ ሀገር ሉዓላዊነቱ ተደፈረ ሲባል ሀገሩ በሌሎች ተፅዕኖ ስር ወደቀ፣ ክብሩ ተዋረደ፣ ነፃነቱ ተገፈፈ እና ከአራቱ መሠረታዊ የመንግሥት ባህሪያት መካከል አንዱ የሆነውን ነፃነቱን አጣ ማለት ነው የሚሉት አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ናቸው፡፡ እንደ አምባሳደር አክሊሉ ገለጻ አራቱ መሰረታዊ የመንግሥት ባህሪያት የሚባሉትም ዓለም አቀፋዊ እውቅና፣ መንግስታዊ መዋቅርና አደረጃጀት፣ ከውጭ ኀይሎች ቁጥጥርና ተፅዕኖ ነፃ መሆን እና የሕዝብ መኖር ናቸው ይላሉ።
የሉዓላዊነት ሃሳብ የሀገረ መንግሥት አንዱ መገለጫ መንግሥት ያወጣውን ሕግ በዜጎቹ እና በሀገሩ ላይ ያለከልካይ እና ያለተቀናቃኝ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው ፍጹማዊ የሆነ ሕጋዊ ሥልጣን እንዳለው ማሳያ ነው የሚሉት አምባሳደሩ፤ ዲፕሎማሲ የመንግሥትን የመፈጸም አቅም ከሚያሳኩ መንገዶች አንዱ ነው ይላሉ፡፡ ዲፕሎማሲም አስቀድሞ ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን መገመት የመቻል ጥበብ፣ የስለላና የመረጃ አቅምን ማጎልበት፣ ሊከሰት የሚችለውን ፈተና የመቋቋም ጥበብ ነው ብለዋል።
አሁናዊው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱ የገጠሟትን ዙሪያ መለስ ፈተናዎች ለመቋቋም የሚችል አቅም መፍጠር ይኖርበታ ያሉት አምባሳደሩ፤ ፐብሊክ እና ዲጂታል ዲፕሎማሲው የውጭውን ዓለም ጣልቃ ገብነት የመቋቋም አቅም እንዲፈጥር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous articleበኩር ጋዜጣ – ጥቅምት 21/2015 ዓ.ም ዕትም
Next article“የባሕር ዳር ከተማን መዋቅራዊ ፕላን በማስጠበቅ ከተመዋን ውብና ለነዋሪዎቿ የምትመች ለማድረግ እንሠራለን” ዶክተር ድረስ ሳህሉ