
ጅጌ የኅብረትና የትብብር ማሳያ ነው፡፡ ስያሜያቸው ይለያይ እንጂ በተለይም በአርሦ አደሮች የሥራ ክዋኔ የሚተገበሩ ኅብረታዊ የመረዳዳት እሴቶች በየአካባቢው አሉ፡፡ በአንዳንዶች አካባቢ ደቦ፣ በሌሎች ደግሞ ወንፈል እና ሌሎችም ስያሜዎች አሉት የመተባበር እና ሥራን የማቀላጠፍ የአርሦ አደሮቹ መልካም ግንኙነት፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ላይ ተገኝተናል፤ አርሦ አደሮቹ በልባዊ የትብብር መንፈስ በየሰብል ማሳዎች ላይ ተሰማርተዋል፤ያሰባሰባቸው ደግሞ ጅጌ ነው፤ የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አርሦ አደሮች የሚረዳዱበትና የሚደጋገፉበት ባህል:: ጅጌ- ‹‹ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› የሚለው የአበው አባባል በተግባር የሚገለጽበት የአንድነት ሃይልነት ምስክር ነው፡፡
ያ ስብስብ፣ ድካምን በሚያስወግዱ፣ መንፈስን ዘና በሚደርጉ ስነ ቃሎች እና ዘፈኖች ሲታጀበ ሰብሉን በምን ያህል ፍጥነት እንደሰበሰቡት ሳይታወቃቸው ሥራቸውን ያቀላጥፍላቸዋል፡፡ በጋራ የመሥራቱን ፋይዳም ከፍ ያደርግላቸዋል፡፡
“አይዞሽ ማጭዴ፣ ማጭዴ ኮልባ፣
አበላሻለሁ ማታ በተልባ፡፡” የሚሉና ሌሎች ስነ ቃሎችን አርሦ አደሮቹ ለሥራው ማቀላጠፊያነት ይጠቀማሉ፡፡
በጅጌ ባህል መሠረት ምንጃር ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አርሦ አደሮች ተሰባስበው ሰብላቸውን እየሰበሰቡ ነው፡፡ በወረዳው ክትቻ በተባለ ቀበሌም በኩታ ገጠም የተዘራውን የጤፍ ማሳ በዚህ የመረዳዳት ባህል መሠረት ሰብስበዋል፡፡ (ኩታ ገጠም የሰብል አመራረት ዘዴ ተመሳሳይ የሰብል ዓይነቶችን በአንድ አካባቢ መዝራትን የሚገልጽ ነው፡፡) በአንድ ቀንም 200 ሄክታር የጤፍ ሰብል እንደሰበሰቡ ተመልክተናል፡፡
የአካባቢው አርሦ አደሮች ለአብመድ እንደተናገሩት ባህላዊ ትብብሩ የሕዝቡን ትስስር ከማጠናክሩም በላይ ሰብሉን በወቅቱ ለመሰብሰብ አስችሏቸዋል፡፡ ይህም የድካማቸው ፍሬ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት እያደረገላቸው ነው፡፡
አሁን በአካባቢው የተለያዩ ቀበሌዎች የሰብል ስብሰባው ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በማኛ ጤፍ ምርት በሚታወቀው የምንጃር ሽንኮራ ወረዳ በዚህ የምርት ዘመን 97 ኩታ ገጠም ማሳዎች በጤፍ እንደተሸፈኑ ታውቋል፡፡
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ይትባረክ አብርሃም ሰብሉ ለብክነት ሳይጋለጥ እየተሰበሰበ እንደሆነ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ጅጌ ደግሞ ለዚህ ፍቱን መፍትሔ ነው፡፡ ምንጃር ላይ በሄክታር ከ25 እስከ 28 ኩንታል ጤፍ እንደሚመረት ከአርሦ አደሮቹ ሰምተናል፡፡
አርሦ አደሮቹ ጅጌን በወቅታዊ ሥራዎች ከማሰባሰቡ እና ሥራን ከማሳካቱ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ የመተጋገዝ ባህሉ በህብረተሰቡ የጋራ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመወሰንና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያስችላቸው በሰብል አሰባሰቡ ላይ የተገኙ አርሦ አደሮች ተናግረዋል::
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው፡፡ የአሁኑ የሰብል ቁመና ምልከታም የታቀደውን ምርት ማግኘት እንደሚቻል አመላካች እንደሆነ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል::
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ- ከምንጃር ሸንኮራ ወረዳ
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ)