
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በሀገሬው ሰው ዘንድ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ቀያሽ የኑባሬ ታሪኳ አዳሽ ተደርገው ይወሰዳሉ። ንጉሠ ነገሥቱ ስልጣኔ የጠማቸው መሪ ናቸው ሲባል መገለጫዎቹ ባቡር ስላስገቡ ውኃ በመዘውር ስለሳቡ፣ እህልን ከወፍጮ ስላዋደዱ በስልክ ንግግር ስላለማመዱ፣ ወሰን ስላጸኑ ሀገር ስላቀኑ እና የዘመኑን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስላስተዋወቁ ከዘመኑ አስተሳሰብ ብቻቸውን ከፍ ብለው ስለላቁ ብቻ አልነበረም።
የታላቁ ጥቁር መሪ ስልጣኔን መሻት ከቁስ ሁሉ ይልቃል ከዘመኑ እሳቤም ይመጥቃል። የምኒልክ ስልጣኔ በዋናነት የሚገለጸው በሀገሩ የውስጥ ጉዳይ የነቃ እና የበቃ፤ የሰለጠነ እና የተካነ ስልጡን ትውልድ ስለፈጠሩ ነው ይባላል። እምየ ምኒልክ ለሀገራቸው እና ለአህጉራቸው የሰለጠነ ሰው ሰርተው፤ ብቁ ትውልድ ገንብተው ያለፉ ጥበበኛ እና አንጥረኛ መሪ ስለመኾናቸው ታሪክ በሰፊው ይነግረናል።
ሰው አንጾ የሠራ፣ ትውልዱን በአስተሳሰብ የገራ እና የተሻለውን መንገድ የመራ ባለራዕይ ንጉስ ደግሞ ስልጡን መባል ያንሰዋል። ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የስልጣኔ መሳለጥ፤ የታላቅ ሀገር መገለጥ ምክንያቱ በአግባቡ የተሠራ በቅንነት የተገራ ትውልድ መፈጠሩ ነው። “ሀገር ማለት ሰው ነው” እንዳለ ባለቅኔው አዎ! አጼ ምኒልክም ሰው ላይ እምነት ጥለው፤ ትውልዱ ላይ አነጣጥረው ስልጡን ማኅበረሰብ ሰርተዋል።
ስልጡን ሕዝብ ደግሞ ሀገሩን በሚገባ ያውቃል ሉዓላዊነቱን ይጠብቃል። የነቃ ማኅበረሰብ ሀገሩን ከጥቃት ወገኑን ከውርደት ይታደጋል። በሀገሩ ጉዳይ ያውም በዚያ ዘመን “እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ” በዐይን ጥቅሻ የሚግባባ ትውልድ መገንባት በእርግጥም ታላቅ የሚባል ስልጣኔ ነው።
የበዛ እምነት በሚስተናገድባት፤ ብዙ ቋንቋ በሚነገርባት ጥንታዊት ሀገር ውስጥ ልዩነትን አጥብቦ በአንድ ቦታ ተሰባስቦ ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም መቻል መሪውን ጥበበኛ ትውልዱንም ተዓምረኛ ያሰኛል። አጼ ምኒልክ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብለው በሀገሩ ጉዳይ ከልዩነቱ የሚሻገር ለሆዱም የማያድር፤ ለክብሩ ሟች ለነጻነቱም ሞጋች፤ ለባንዲራው ቅድሚያ የሚሰጥ መሪዎቹንም የሚያዳምጥ፤ በሥነ ሥርዓት የሚያምን ቅድሚያ ልሰዋ ብሎ የሚለምን ትውልድ አዘጋጅተው ነበር።
ከ127 ዓመታት በፊት የዓለምን የጦርነት ታሪክ የቀየረ፤ የኀይል ሚዛንን የዘወረ የድል ታሪክ መነሻው እና መጠንሰሻው ዛሬ ነው፡፡ “ዘመቻየ በጥቅምት ነውና የሽዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከትተህ ላግኝህ” የሚል አዋጅ ያስነገሩት አጼ ምኒልክ ጥቅምት 18 ወረኢሉ ገቡ፡፡ ወረኢሉም ንጉሰ ነገስቱን እና ጦራቸውን ለ14 ቀናት ያክል አስተናገደች፡፡ ወረኢሉ የአድዋ ተራሮችን ለድል አዘጋጀች ሮምንም ለሽንፈት አጨች፡፡ ወረኢሉ ሮም ድረስ ዘልቃ ትታዎቃለች፡፡
እስከ አሁንም ድረስ “የሃበሻ ቀጠሮ” በሚባልባት ሀገር ያውም በዚያ ዘመን በአንድ አዋጅ ቀጠሮ ጠብቆ ትዕዛዝ አውቆ ወረኢሉ እንዴት መክተት ቻለ? “ስንቅህን በአህያህ አመልክን በጉያህ” የተባለ ዘማች በቀጭን ትዕዛዝ እንዴት ለሥርዓት ተገዥ እና ስልጡን ሆነ፡፡ ንጉሠ ነገሥት አጼ ምኒልክ በእርግጥም “ሰው ሰርቷል” ማለት ነው፡፡ በጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰፊ እና ጥልቅ ጥናት ያደረጉት ሪቻርድ ፓንክረስት “አጼ ቴዎድሮስ ሥርዓት አቀና፤ አጼ ምኒልክ ደግሞ ሰው ሠራ” የሚሉን እውነት ነው፡፡
የዛሬይቱ ኢትዮጵያም ከቀጠሮ የሚቀድም፤ ልዩነቱን አጥብቦ በአንድ የሚቆም ትውልድ ያስፈልጋታል፡፡ ምኒልክን የፈተኑት የውስጥ ባንዳዎች የውጭ ወራሪዎች አሁንም ድረስ ሀገሪቱን በተለያየ መንገድ እየፈተኗት ነው፡፡ አሁናዊቷ ኢትዮጵያ ፈተናዋ ዘርፈ ብዙ ነው፤ የትውልዱን ዘርፈ ብዙ ዘመቻም ትሻለች፡፡ ወረኢሉ ላይ ተሰባስቦ አድዋ ላይ ድል የሚያደርግ ትውልድ፤ እስከ ሮም ዘልቆ የሚሰማ የድል ብስራት ዜማ ኢትዮጵያ ትሻለች፡፡
በታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J