
ጥቅምት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ በርካታ ትምህርቶች የተገኙበት እንደነበር የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአግባቡ ከተመሩ፣ ከቆረጡና ጥረት ካደረጉ የትኛውንም ተልዕኮ መወጣት እንደሚችሉ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡
ሕዝብ ሲያማርርባቸው የነበሩ ጉዳዮችን መንግሥት ለማረም ሲነሳና ጥረት ሲያደርግ ድጋፍ እንደሚሰጡ በተጨባጭ የተረጋገጠበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ እንደ ሀገር ሕዝቡ በሚያማርርባቸው የተደራጀ ሌብነት፣ መልካም አሥተዳደር እጦት፣ ለመንግሥት አገልግሎት እጅ መንሻ መጠየቅ ላይ እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ ሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃ ላይ የሚታዩ ግድፈቶችን ለማስተካከል ሕዝቡን ከጎናችን ካሰለፍን ትርጉም ባለው መልኩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ትምህርት ተወስዶበታል ብለዋል፡፡
የፈተና አስፈጻሚዎች ከሚያስተምሩበት ተቋም ውጪ መመደባቸው ኢትዮጵያውያን አሁንም የተሳሰርንበትና የተጋመድንበት ጠንካራ ማኅበራዊ ትስርስር ያለን መሆኑን የተረዳንበት ነበርም ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡፡
አጠቃላይ ሂደቱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ቅቡልነት መልሶ ለመገንባት እድል የተፈጠረበት መሆኑን ጠቅሰው በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ መተግበርና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለሀገር ክብር በትግል እናብር

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ