“ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት ለተዋደቁ የሰራዊት አባላት ቋሚ መታሰቢያ ሊኖር ይገባል” ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ

171
ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት ለተዋደቁ የሰራዊት አባላት ቋሚ መታሰቢያ ሊኖር እንደሚገባ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንን ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀንን በማስመልከት በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የተዘጋጀና እስከ ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት በይፋ ተከፍቷል።
በአውደ ርዕዩ መክፈቻና ጉብኝት ላይ የተገኙት የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ ለኢዜአ እንደገለጹት መሰል ዝግጅቶች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ከፍተኛ ትርጉም አላቸው።
የኢትዮጵያ ሰራዊት በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በአግባቡ ስለመደራጀቱ ከታሪክ መረዳታቸውን አስታውሰው፤ በወቅቱ የተደራጀው ጦር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ኖሮት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያገኘ እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ላይ የሰራዊት ቀን ታሪክን መነሻ አድርጎ በመከበር ላይ በመሆኑ ለሀገሩ እየተዋደቀ ላለው ሰራዊትና ለሁላችንም ደስታን የፈጠረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሰራዊቱ በየትኛውም አጋጣሚ በጀግንነት መስዋእትነት በመክፈል ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት ለተዋደቁ የሰራዊት አባላት ቋሚ መታሰቢያ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት።
የሰራዊቱ የጀግንነት ታሪክ በመንግሥት ወይም በሰዎች መለዋወጥ የማይናወጥ ሆኖ በቋሚነት የሚወሳ ክብርና ዕውቅና ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚከፍለው መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በመሆኑ ዘመን የማይሽረው አኩሪ ገድል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ፤ ከመስመራዊ መኮንንነት እስከ ከፍተኛ መኮንንነት ሰራዊቱንና ሀገራቸውን ያገለገሉ ታላቅ ባለውለታ መሆናቸው ይታወቃል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous article“የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ ተልዕኮ አሸባሪው ወያኔ ሰብዓዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሐን ዜጎች ነጻ ማውጣት ነው” የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ
Next articleMaxxansa gaazexaa Hirkoo Onkoloolessa 15/2015