
ጥቅምት 15/ 2015 ዓ.ም (አሚኮ) “የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ ተልዕኮ የሽብር ቡድኑን ወታደራዊ አቅም ማዳከምና ቡድኑ ሰብዓዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሐን ዜጎች ነጻ ማውጣት ነው” ሲል የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።
የሽብር ቡድኑ “ንጹሐን ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል” በሚል በርካታ ያቀናበራቸው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት መገኘታቸውን አመልክቷል።
አሸባሪው ወያኔ በጦር ሜዳ የገጠመውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፋፈን በቁጥጥሩ ሥር ያሉ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም “ንጹሐን ዜጎች እየሞቱ ነው በሚል ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲፈጠር ሙከራ እያደረገ ነው” ሲል የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በመግለጫው አስታውቋል።
የሽብር ቡድኑ “የንጹሐን ዜጎች ሞት” ሐሰተኛ ትርክት ዓላማ “ለአደጋ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ጉዳትና ሞት ዓለም አቀፍ ቁጣና ውግዘት ያመጣልኛል” የሚል እንደሆነ አመልክቷል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ ተልዕኮ የሽብር ቡድኑን ወታደራዊ አቅም ማዳከምና ቡድኑ ሰብዓዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሐን ዜጎች ነጻ ማውጣት እንደሆነ ገልጿል።
ሁሉም ተዋጊ አሐዶች በግጭት ቀጠናዎች የንጹሐን ዜጎችን ጥበቃን አስመልክቶ በቂ ሥልጠና መውሰዳቸውንና በተለያዩ ቀደምት የግዳጅ አፈጻጸማቸው ስኬታ መሆኑን ማስመስከራቸውን አመልክቷል።
“አሸባሪው ወያኔ ንጹሐን ዜጎችን አደጋ ላይ በመጣል ሐሰተኛ ተጎጂዎችን በመፈብረክ” በርካታ ያቀናበራቸው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት መገኘታቸውን ገልጿል።
በሌላ በኩል “የአየር ድብድባ ተፈጽሟል በሚል ከሰሞኑ ሲሰራጩ የነበሩ ምስሎች አግኝቻለሁ” ያለው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ምስሎቹ ሐሰተኛና በተባሉት ቦታዎች ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱን አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!