
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር ይጌጣል፣ በሀገር ደስታ ይታያል፣ በሀገር ይከበራል፣ በሀገር ይኮራል። ሀገር የሌላቸው በበዓዳን ሀገር ተንከራትተዋል፣ ሀገር የሌላቸው በወገን ፊት ማጌጥን፣ በዘመድ ፊት መደሰትን ናፍቀዋል፣ ሀገር የሌላቸው መዳረሻ አጥተው ተንከራትተዋል። ነጻነት ርቋቸው በባርነት ታስረዋል። ሀገር የሌለውን ያገኘ ሁሉ ይረግጠዋል፣ የተነሳ ሁሉ ይገፋዋል፣ ክብሩን ዝቅ ያደርገዋል፣ ሀገር የለሽ እያለ ያሳድደዋል።
ሀገራቸውን ያጡት፣ ነጻነታቸውን የተነጠቁት ቢጠማቸው የሚጠጡት፣ ቢርባቸው የሚጎርሱት፣ ቢደክማቸው የሚያርፉበት በሌለበት፣ ለዓይን ተስፋ በማይገኝበት ምድር እየተንከራተቱ የበረሃ ሲሳይ ኾነው ቀርተዋል። ሀገር የሌላቸው በጭንቅ ዘመን ዋይታ እያበዙ አልፈዋል፣ ሀገር የሌላቸው እየተሳደዱ ተገድለዋል። ማረፊያ፣ መጠጊያ አጥተው በስቃይ አለንጋ ተገርፈዋል። ሀገራቸውን ያስከበሩት፣ ነጻነታቸውን ያስጠበቁት ግን በኩራት ተራምደዋል፣ የፈለጉትን አድርገዋል።
ለሀገር ክብር ሲሉ የሞቱት፣ ለነጻነት ሲሉ የተሰዉት ልጆቻቸውን ባለ ሀገር አድርገዋል። በነጻነት ኖረው ነጻ ሀገር ነጻ ትውልድ አፍርተዋል። ስለ ከበረች ሀገራቸው፣ ተስፋ ስለኾነች ሠንደቃቸው፣ በምንም ስለማይለውጧት ክብራቸው፣ ዝንፍ ስለማትል ወርቃማ ታሪካቸው ሲሉ ደም አፈሰሱ፣ አጥንት ከሰከሱ። በደማቸው ነጻነት፣ በአጥንታቸው ማንነት አፀኑ።
ኢትዮጵያ ኾይ አንቺን የነኩሽ ዕለት ጠላቶችሽ ወዮላቸው፣ ኢትዮጵያ ኾይ አንቺን የተዳፈሩት ምን ይኾን የሚያድናቸው እያሉ ይነሳሉ። በኢትዮጵያ ላይ የተነሱትን ሁሉ ይመታሉ። ኢትዮጵያ ኾይ ብንከዳሽ የጠበቀሽ፣ ያከበረሽ፣ የከለለሽ፣ ያበረታሽ፣ ያፀናሽ፣ ከሁሉም ያስቀደመሽ፣ ሁሉንም የሰጠሽ፣ ለምስክርነት ያስቀመጠሽ አምላክሽ ይክዳን፣ መቀበሪያ አፈር ይንሳን እያሉ የሚነሱት ልጆቿ አስከብረዋት ኖረዋል።
በየዘመናቱ አያሌ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ተነስተዋል፣ ኢትዮጵያ የምትለውን፣ ከምንም በላይ ሲጠሯት የምትጣፍጠውን፣ ልብን እየነዘረች በሐሴት የምታሰግረውን ስም ሊያጠፏት፣ ነጻነቷን ሊነጥቋት፣ ታሪኳን ሊያጠፉባት፣ ወግና ሥርዓቷን ሊያሳጧት፣ ሃይማኖቷን ሊያረክሱባት ብዙዎች ተነስተዋል። ጦር ሰብቀው፣ ወታደር አዝምተዋል። በየወንዙ ዳር እየተማማሉ ሊወጓት ተነስተዋል።
ጀግና እየወለደች፣ ጀግና እያሳደገች፣ በጀግና ትጠበቃለች እና ኾኖለት ያሸነፋት፣ ገፍቶ የጠላት፣ እንደ ምኞቱ ከታሪክ መዝገብ ላይ የሰረዛት፣ ያሰረዛት አልተገኘም። እናጥፋሽ ያሉት ጠፍተው፣ እንጣልሽ ያሏት ወድቀው፣ እናዋርዳት ያሉት ተዋርደው፣ እናሸንፋት ያሉት ተሸንፈው ይመለሳሉ እንጂ። እርሷ ከድል ላይ ድል እየጨማመረች በታሪክ መዝገብ ከፍ ትላለች። እርሷ ምቀኞቿን እየጣለች በአሸናፊነት ትራመዳለች።
ጠላት በተነሳባት ጊዜ ልጆቼ ከዳር ዳር ይጠራራሉ፣ ጠላት ተነሳበት ወደ ተባለበት አቅጣጫ በአንድነት እና በጀግንነት ይጓዛሉ። የእነርሱ የማሸነፊያቸው ምስጢር አንድነታቸው እና ፍቅራቸው ነውና በአንድነት እና በፍቅር ይገሰግሳሉ፣ በአንድነት ክንድ ይሰነዝራሉ፣ በአንድነት ክንድ ያደቅቃሉ፣ በአንድነት ክንድ ጠላቶቻቸውን ይጥላሉ።
ለነጻነት ከሁሉም አስቀድሞ ፍቅርና አንድነት ይኖር ዘንድ ግድ ይላል። ፍቅር እና አንድነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻቸውን መትተዋል፣ ድል አድርገው ሠንደቃቸውን አውለብልበዋል። ፍቅርና አንድነት የጠላት ጠመንጃ የማይጥሰው ፅኑ መዳኛ ነውና።
ያለ ነጻነት ከመኖር በነጻነት መሞት ይሻላል እንዲሉ ጀግኖች ለነጻነት እና ለሀገር የሚሰስቱት የለም። እስከመጨረሻው ሕቅታ ድረስ ይሰጣል እንጂ። ጀግኖች ለነጻነት ሲሉ መከራውን ረስተው፣ ሞትን ንቀው በጀግንነት ታገሉ፣ ለእማማ ኢትዮጵያ ደማቸውን አፈሰሱላት፣ አጥንታቸውን ከሰከሱላት። በደማቸው አስከበሯት፣ በደማቸው ፍሳሽ አኮሯት፣ ዳግም ከጠላት በላይ አዋሏት፣ ስሟን ከፍ ከፍ አደረጉላት።
አንድ ኃይል አለ የጠላቶችን ሕልም ሁሉ መና የሚያስቀር። ይህም ኃይል በኢትዮጵያዊነት፣ በአንድነት፣ በጀግንነት፣ በጽናት መቆም ነው። ኢትዮጵያ እልፍ ጊዜ ተፈትናለች፣ ፈተናዎቿን ግን በድል ተሻግራቸዋለች። ፈታኞቿንም ጥላቸዋለች። እንዳይነሱ አድርጋ ሸኝታቸዋለች። በውጭ በወራሪዎች ዘመን በባንዳዎች የተወጉት በአንድነት ታግለው ድል አድርገዋል። ዛሬም በአንድነት የተነሱ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ወያኔ አማካኝነት የተነሳውን እልፍ ጠላት ድል ይመቱታል። ጠላቶች እንኳን መልዕክት ልከው ራሳቸው መጥተው፣ ጦር አዝምተውም ኢትዮጵያን አላሸነፏትም። ወደፊትም አያሸንፏትም። ለምን ለሀገር ክብር ሞትን የሚንቁ ጀግና ልጆች አሏትና።
ዛሬም ጀግንነት እና ቃል ኪዳን ከቀደምት ጀግኖች አባቶች የተቀበሉት የኢትዮጵያ ጀግኖች በኢትዮጵያ ላይ እግሩን ያነሳውን ለመቅጣት፣ በዱር በገደል፣ በተራራ በሸንተረር ይመላለሳሉ። ኢትዮጵያን ያስከብሯት ዘንድ በጀግንነት ከጠላት ጋር ይዋደቃሉ። የተሰጣቸው ቃል ኪዳን፣ የተቀበሉት አደራ የማይሻር ነውና በጀግንነት ኢትዮጵያን ይጠብቃሉ። መከበር ብቻ የሚያምርብሽ፣ ድል ማድረግ ብቻ የተሰጠሽ፣ በአሸናፊነት የነገስሽ፣ ከጠላቶችሽ ልቀሽ የተገኘሽ እማማ ኾይ ለዘለዓለም ክበሪ። በጽናት ኑሪ።
ክብር ስለ ኢትዮጵያ ሞትን ለናቁት፣ ድካሙን ለረሱ ጀግኖች!
እንኳን ለመከላከያ ሠራዊት ቀን አደረሳችሁ!!
በታርቆ ክንዴ (በድጋሚ ተሻሽሎ የቀረበ)
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
