16ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀመረ።

145
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሀ ሻወል በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ጅቡቲ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት አንስተዋል። የጋራ ስብሰባውም በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚወያይ ጠቁመዋል።
የጅቡቲ ልኡክ መሪ አምባሳደር መሀዲን ኦብሲ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገሮች በባህል፣ ቋንቋና በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በመድረኩ ሙያተኞች የሁለቱን ሀገሮች የምጣኔ ሀብትና ሌሎች ዘርፎችን የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸውና የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ተወያይተው መፍትሔ ያመላክታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
በምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ እንዲሁም በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ጉዳዮች የትብብር መስኮችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከር በስብሰባው ለውይይት የተያዙ አጀንዳዎች ናቸው።
በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች፣ በምጣኔ ሀብት ትስስር፣ በህግና ፍትህ፣ በስደትና በፖለቲካ የትብብር መስኮች እና ሌሎች ጉዳዮች በሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ በምጣኔ ሀብት ዘርፍም በንግድ፣ በግብርና፣ በውኃና ኢነርጂ እንዲሁም በሳይንስ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ሀገሮች ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የተያዘው መርሃ ግብር ያሳያል።
በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ጉዳዮች የትብብር መስኮች ወደብና ተያያዥ ጉዳዮች፣ የባቡር ትራንስፖርትና ማሪታይም ለውይይት ከተያዙ አጀንዳዎች ውስጥ ይገኛሉ።
ስብሰባው ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ሁለቱ ሀገሮች መሰረተ ልማትን ጨምሮ በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።
ኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱን አገሮች በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያለመ ነው።
15ኛው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በጅቡቲ ከተካሔደ በኋላ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ መቆየቱም ተጠቅሷል። ዘገባው የኢዜአ ነው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
Previous articleየመጀመሪያውን ዙር የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚዳስስ “የእሳት ቀለበት” የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል።
Next article❝ስለ ኢትዮጵያ ሞትን ንቀዋል፣ ድካሙን ረስተዋል❞