የመጀመሪያውን ዙር የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚዳስስ “የእሳት ቀለበት” የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል።

247

ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመከላከያ ሚኒስቴር ጥናትና ምርምር ማዕከል የወታደራዊ ንድፈ ሐሳብ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የመጽሐፉ ዝግጅት ኮሚቴ ዋና አሥተባባሪ ኮሎኔል ሙላት ደሳለኝ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሠራዊት ቀንን በማስመልከት “የእሳት ቀለበት” በሚል የተዘጋጀው መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል።
መጽሐፉን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚጠጋ ጊዜ መውሰዱን የገለጹት ኮሎኔሉ፤ መጽሐፉ በሦስት ምዕራፎች የተቀነበበ መሆኑን አንስተዋል።
“የእሳት ቀለበት” መጽሐፍ የድርጊቱን ተዋናዮች እስከ ታች ድረስ ወርዶ በመጠየቅ የተዘጋጀ እንጂ በልብ ወለድ መልኩ የተፃፈ እንዳልሆነ በመግለፅ፤ መረጃዎች የሚሰባሰቡበት መንገድ ትኩረት ተሰጥቶ በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም የጦር ክፍሎች የመረጃው ምንጭ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም መሠረት ከሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል በመሄድ በወቅቱ የነበሩ አራት ዕዞችን ያማከለ 11 መኮንኖች በማሠማራት ከሁሉም የጦር ክፍሎች መረጃ ከወታደር እስከ ከፍተኛው አመራር ድረስ መሰብሰብ መቻሉን ኮሎኔል ሙላት ገልጸዋል።
በሂደቱም ጦርነቱን የመሩ ከጄኔራል እስከ ኮሎኔል ማዕረግ ደረጃ ያላቸው 44 አመራሮችን በተዘጋጀ ቃለ መጠይቅ መሠራቱን እና በጥቅሉ 1 ሺህ 685 ሰው የተሳተፈበት ውይይት ተደርጎ መረጃ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል። ሌሎች ተጨማሪ የመረጃ ምንጮችም እንደ ግብዓት መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
‟የእሳት ቀለበት” መጽሐፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሕወሓት ማኒፌስቶ ዙሪያ ሰፊ መንደርደሪያ የያዘ፣ ዕኩይ ተግባሩ በድንገት የመጣ ሳይሆን ገና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በቀረጸው ማኒፌስቶ የተያዘ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ሰፊ ትንታኔ እንዲይዝ ተደርጎ ተዘጋጅቷል።
ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ሕወሓት ከለውጡ በኋላ ምን ዓይነት እንቅፋት የሆኑ ሥራዎችን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ ይሠራ እንደነበር፣ በተለይ በሕዝቦች መካከል ይፈጥር የነበረው የጸጥታና ደኅንነት ችግርን እንዴት ያስፋፋ እንደነበር፣ ሰሜን ዕዝን ለምን መካድ እንዳስፈለገውና በክህደቱ ሳምንታት በሠራዊታችን ላይ የፈጸመው ግፍና በደል በዝርዝር የቀረበበት ሰፋ ባሉ ንዑስ ርዕሶች የተደራጀ ምዕራፍ ነው።
ምዕራፍ ሦስት ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከአፈና ራሱን አላቆ የመልሶ ማጥቃት በመሰንዘር በ17 ቀናት ጦርነት ትግራይን እንዴት ከጁንታው መንጋጋ እንዳላቀቀና የትግራይን ሕዝብ ወደ ተለመደው ማኅበራዊ ኑሮ እንዲመለስ ማድረግ መቻሉን ያሳያል። በሂደቱም የጦር ክፍሎች ያደረጉት ተጋድሎና ገድል በዝርዝር የሚያሳይበት ሆኖ፣ በስትራቴጂና ኦፕሬሽናል ደረጃ ከተደመሰሰ በኋላ ትግራይ በቆየባቸው ስድስት ወራት “የሕግ ማስከበር ዘመቻውን” ብቻ የያዘ ታሪክ መሆኑን ያሣያል።
የመጽሐፉ ዝግጅት አሥተባባሪ ኮሎኔል ሙላት፣ “የእሳት ቀለበት” መጽሐፍ ድርሰት ሳይሆን እውነተኛ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የሆነና በውስጥ የሚጠቀሱ ማንኛውም ሥሞችና ቦታዎች የገድሉ ባለቤት ሠራዊታችን መሆኑን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

Previous article“ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ኅልውና እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በሚከፍለው መሥዋዕትነት በድል ወደ ግቡ እየተቃረበ ነው”፦ የመከላከያ ሠራዊት
Next article16ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀመረ።