“ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ኅልውና እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በሚከፍለው መሥዋዕትነት በድል ወደ ግቡ እየተቃረበ ነው”፦ የመከላከያ ሠራዊት

167
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ኅልውና፣ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ በወደር የለሽ ጀግንነት በሚከፍለው መሥዋዕትነት በድል ላይ እየተረማመደ ወደ ግቡ እየተቃረበ ነው” ሲል የመከላከያ ሠራዊት ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን የሚከበረውን የሠራዊት ቀንን ምክንያት በማድረግ “የጥንካሬያችን ምንጭ ሕዝባችን ነው!!” በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል።
ኢትዮጵያ በሠራዊት ግንባታ ታሪክ ረጅም ዘመን ያስቆተረች መሆኗን የገለጸው ሠራዊቱ፣ ሆኖም እንደተቋም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ያቋቋመችበትን ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም መነሻ በማድረግ የሠራዊቱ ቀን በየዓመቱ እንዲከበር መወሰኑን አመልክቷል።
አሁን ላይ ሀገራችን እና ተቋማችን የጀመሩት የሠራዊት ግንባታ አቅጣጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት የሚመጥን፣ በቀጠናው ላለብን ከፍተኛ ኃላፊነት ብቁ የሆነ፣ የሕዝብ አመኔታን የተጎናፀፈ፣ ወታደራዊ እውቀት እና ክህሎትን የጨበጠ፣ በፈጠረው አስተማማኝ ዝግጁነት ጦርነትን በሩቁ ማስቀረት የሚችል፣ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተገቢውን ሚና የሚጫወት ኃይል የመፍጠር ራዕያችን ሲሆን ተቋማችን መከላከያም ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት እየተወጣው ይገኛል ብሏል መግለጫው።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብራክ የወጣ ለሕዝብ ደኅንነት እና ለሀገር ሉዓላዊነት የአካል እና የሕይወት መሥዋዕትነት የሚከፍል ብሔራዊ ኃይል መሆኑን አመልክቷል።
የሠራዊታችን የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና፣ ከፍታ እና የድል ምንጩ ጠንካራው እና ነፃነቱን እና ብሔራዊ ክብሩን አሳልፎ የማይሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ሲልም ገልጿል።
የዘንድሮውን ታሪካዊ በዓል የምናከብረው ኅልውናችንን ለማስጠበቅ ተገድደን የገባንበት አስከፊ ጦርነት ውስጥ ሆነን ነው ያለው መከላከያ ሠራዊት፣ ነገር ግን ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ኅልውና፣ ሉዓላዊነት፣ የብሔራዊ ጥቅም እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በወደር የለሽ ጀግንነት በሚከፍለው መሥዋዕትነት በድል ላይ እየተረማመደ ወደ ግቡ እየተቃረበ መሆኑን አረጋግጧል።
“ከደጀን እስከ ግንባር የሕዝባችን የማይነጥፍ አጋርነት እና ድጋፍ ምክንያቱ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ተቋጭቶ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገት እና ብልጽግናችን እንዲቀጥል ያለው እጅግ ከፍተኛ መሻት ነው” ሲልም በመግለጫው አመልክቷል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous article“አትንኳት፣ ኢትዮጵያ ከምንም ከማንም በላይ ናት”
Next articleየመጀመሪያውን ዙር የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚዳስስ “የእሳት ቀለበት” የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል።