“አትንኳት፣ ኢትዮጵያ ከምንም ከማንም በላይ ናት”

113
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/ 2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን አትንኳት መከፋቷ የሚከፋቸው፣ መነካቷ የሚያማቸው፣ እንቅልፍ የሚነሳቸው ልጆች አሏት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት ለክብሯ ደም የሚያፈስሱላት፣ ለክብሯ አጥንት የሚከሰክሱላት፣ ሕይወት የሚገብሩላት ልጆች አሏት፡፡ ኢትዮጵያን አትንኳት ቁጣዋ ይጥላችኋል፣ ሰይፏ ይቀላችኋል፣ ማዕበሏ ይውጣችኋል፣ ክንዷ ያደቅቃችኋል፡፡
ኢትዮጵያን አትንኳት ከሕይወታቸው የሚያስበልጧት፣ ከማንም ከምንም በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጓት፣ አጥር ኾነው ዙሪያ ገባውን የሚጠብቋት፣ መሠረት ኾነው የሚያጸኗት፣ ምሰሶ ኾነው የሚያቆሟት፣ ማገር ኾነው የሚደግፏት፣ መከራ የማያስቆማቸው፣ ጨለማ የማይበግራቸው፣ ቸነፈር የማይገታቸው፣ ውሽንፍር የማያስደነብራቸው፣ ነጎድጓድ የማያስደነግጣቸው ልጆች አሏት፡፡
ኢትዮጵያን ስትነኳት ልጆቿ እንደ ነብር ይቆጣሉ፣ እንደ እሳት ይፋጃሉ፣ እንደ ማዕበል ያደባልቃሉ፣ እንደ መብረቅ ያደርቃሉ፣ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተዋት፣ ኢትዮጵያን ከልጆቿ በላይ እናውቅልሻለን አትበሏት፣ በራሷ ጉዳይ አትግቡባት፣ እርሷ ከራሷም አልፋ ለሌሎች ምልክትና ምሳሌ የኾነች ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የጥቁር ዘር ሁሉ ብርሃን ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የአሸናፊነት ተምሳሌት ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የጨለማ ዘመን ብርሃን ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የሥልጣኔ በር ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የአጥቢያ ኮኮብ ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት ምስክር ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የሰዎች ሁሉ ተስፋ ናት፡፡
እርሷን የነኳት አልቀዋል፣ እርሷን የነኳት ወድቀዋል፣ እርሷን የነኳት አፈር ትቢያ ኾነዋል፡፡ ታሪኳን አይተው ይቀኑባታል፣ እሴቷን አይተው ይመቀኟታል፣ ጽናቷን አይተው ይገረሙባታል፣ ሃይማኖቷን አይተው ይደመሙባታል፡፡ የጠበቀ ሃይማኖት የጠበቃት፣ የከበረ ጀግንነት ያስከበራት፣ የጸና አንድነት ያጸናት፣ ረቂቅ የሆነ ብልሃት ያረቃቃት ናትና በአሻገር የሚያዩዋት ሁሉ ይቀኑባታል፡፡
ዘመን አንስቷቸው፣ ጊዜ ደግፏቸው ጉልበት ያገኙት ሁሉ የክፋት ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ይጥላሉ፣ መክረው ዘክረው ጦር ያዘምታሉ፡፡ ድንበሯን አልፈው የሚፈልጉትን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ማድረግ ያስባሉ፣ ይመኛሉ፡፡ እርሷ በረዘመ የታሪክ ጉዞዋ ያለ ጠላት ውላ አታድርም፤ ጠላቶች ይመክሩባታል፣ ይዘክሩባታል፣ በምን እንደሚያጠፏት፣ በምን እንደሚያሳንሷት፣ በምን ከታሪክ መዝገብ ላይ እንደሚፍቋት ይዶልቱባታል፡፡
የበዙ ጦርነቶች ታወጁባት ሁሉንም አሸነፈቻቸው፣ የበዙ ጠላቶች ተነሱባት ሁሉንም ጣለቻቸው፡፡ ዳሩ እያሸነፈች ትገሰግሳለች፣ እያሸነፈች በታሪክ መዝገብ ላይ ከፍ ከፍ ትላለች እንጂ ጠሏቶቿ ዝም ብለው አይተኙም፣ የአባቱን ሽንፈት ለማካካስ ልጁ ይነሳል፣ ልጁም ይሸነፋል፣ የልጅ ልጁ እያለ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከሚነሱባት ጠላቶቿ ላይ ከድል ላይ ድል እየደራረበች ትቀጥላለች፡፡
ጠላቶች በቀደመው ዘመን ዘመናዊ ሠራዊት አስታጥቀው፣ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ነገሥታቱ፣ ወይዛዝርቱና ጎበዛዝቱ በዓደባባይ ወጥተው፣ ሂዱ ያችን ሀገር ውጓት፣ በእኛ ሥርም አድርጓት ብለው መርቀው ይልኳቸው ነበር፡፡ ሠራዊታቸውም መልካም ምኞቱን ተቀብሎ ባሕር እየከፈለ፣ የብስ እያቋረጠ ይመጣል፡፡ የሸኙት ነገሥታት ሠራዊታቸው ድል እንደሚቀዳጅ በሙሉ ልብ ያምናሉ፣ በቅንጡው ቤተ መንግሥታቸው ተቀምጠው የድል ዜናውን ይጠባበቃሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ሠማይ ሥር የሚሰማው ነገር ግን እንደጠበቁት አይሆንላቸውም፣ የላኩት ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ክንድ ተመትቶ፣ በሰይፋቸው ተቀልቶ፣ በጎራዴያቸው ተበልቶ፣ በሳንጃቸው ተወግቶ እንዳልነበር ይሆናል፡፡ በደስታ የላኩት ወይዛዝርት በሐዘን ያለቅሳሉ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ነገሥታቱ አንገታቸውን ይደፋሉ፡፡ ምነው በቀረብን ሲሉ ይጸጸታሉ፡፡
ኢትዮጵያ በግፍ የመጣባትን መቅጣት፣ በትዕቢት የነካትን መምታት ታውቅበታለችና፣ የሚነኳትን ስታሳፍራቸው፣ የሚደፍሯትን ስታጠፋቸው ኖራለች፡፡
ኢትዮጵያ ጠላት የማይደፍራት፣ ፈሪ የማይኖርባት የጀግኖች ሀገርናትና ክብሯን እንዳስጠበቀች፣ ወሰኗን እንዳስከበረች ዘመናት አልፈው ዘመናት ተተካክተው ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ቀደመው ዘመን ሁሉ ዛሬም ጠላቶቿ ተነስተውበታል፡፡ ጠላቶቿ የበረከቱ ናቸው፡፡ ገሚሶቹ በጉያዋ ተወሽቀው ያደሟታል፣ ይወጓታል፣ መከራዋን ያበዙባታል፡፡ ገሚሶቹ በባሕር ማዶ ኾነው በጉያዋ ተወሽቀው የሚወጓትን ያበረታሉ፣ የኢትዮጵያን እውነት እያዳፈኑ የጠላቶቿን ሐሰት ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ በጉያዋ የተወሸቁት የሽብር ቡድኖች ሲሸነፉባቸው በአሻገር ያሉት ላኪዎቻቸው ዋይታ ያበዛሉ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያበዛሉ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ይታትራሉ፣ የሽብር ቡድኖቹ ሕጻናትን ሲገድሉላቸው፣ ሃብትና ንብረት ሲያውድሙላቸው፣ ንጹሐንንን ሲያሰቃዩላቸው ደግሞ አይዟችሁ በርቱ ግፉበት ይላሉ፡፡ ድጋፋቸውን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሚነሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ ቀደመው ሁሉ ራሳቸው መጥተው ውጊያ አይከፍቱም፣ ራሳቸው መጥተው በኢትዮጵያ ተራራዎችና ኮረብታዎች አይሞቱም፡፡ የዚህ ዘመን ጠላቶች በአሻገር ኾነው ዱላ እያቀበሉ በጉያዋ የተወሸቁ ባንዳዎችን ያበረታታሉ ይደግፋሉ፡፡
ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሀገራቸውን ሳያስደፍሩ የኖሩት ኢትዮጵያውያን ታዲያ በዘመኑ ለተነሳባቸው ጠላትም ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ በጦርነት የመጣውን በጦርነት፣ በሐሰት የመጣውን በእውነት እያጣደፉት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ተዋት ከምንም ከማንም በላይ ናት፣ ኢትዮጵያን ተዋት በደምና በአጥንት የምንጠብቃት ልጆች አለናት እያሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ጠላት ድል አይቀናውም፣ እርሷን የሚያሸንፋት ማንም የለም፡፡ ሁሉም እንደ አመጣጣቸው ይመለሳሉ፣ ሁሉም እንደ አባቶቻቸው ይሸነፋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በድልና በአሸናፊነት ይኖራሉ፡፡
በአንድትህ ጽና ሀገር እንዳትደፈር፣ ኢትዮጵያዊት አሸናፊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ጽናት፣ ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous articleቺርቤዋ ትክምቲ 15 ጌር 2015 ም.አሜታ
Next article“ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ኅልውና እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በሚከፍለው መሥዋዕትነት በድል ወደ ግቡ እየተቃረበ ነው”፦ የመከላከያ ሠራዊት