
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ትላንት ኢትዮጵያውያን የነጻነትን ዋጋ በደማቸው አስከብረዋል፤ ዛሬም እጅ አዙሩን የቅኝግዛት እየታገሉ ነው፡፡
ከትላንቱ የቀጥታ ቅኝ ግዛት እስከ ዘመነኛው የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት (ኒዎ-ኮሎኒያሊዝም) ኢትዮጵያ ለምዕራባውያን የምትመች አልኾነችም፡፡ የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ገብነት እና ከሽብር ቡድኑ ጎን በመኾን በቀጥታም ኾነ በስውር የማገዝን እኩይ ድርጊት በአደባባይ እየታገለች ነው።
ለሁለት ቀናት በመላው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ከተሞች አሸባሪው ወያኔን የሚያወግዝና አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የሚያደርጉት ያልተገባ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል። በውጭ ሀገራት መሰል አላማ ያላቸው ሰላማዊ ሰልፎችም ቀጥለዋል።
“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ” የሕዝባዊ ሰልፉ መሪ ሃሳብ ሆኖ በስፋት ተስተጋብቷል፡፡ በዚህ ሕዝባዊ ሰለፍ ቁልፍ መልእክቶች ተላልፈዋል፤ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ “ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!“ ነው ያሉት፡፡
“…ምዕራባውያን -ሉዓላዊነታችንን አክብሩ፤ የውክልና ጦርነት በቃ፤ ወያኔ የትሮይስ ፈረስ ነው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት መልሕቅ ናት፤ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ለአፍሪካ መቆም ነው…” የሚሉና ሌሎችም መልእክቶች በየከተሞቹ ከፍ ብለው ተስተውለዋል፡፡
እርግጥ ነው ትላንት በኢትዮጵያና የኢትዮጵያን ፈለግ በተከተሉ ሁሉ የከሸፈው የምዕራባውያን፤ የኀያላን ሀገራት የቀጥታ ቅኝ ግዛት መልኩን ቀይሮ ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አፍሪካን ለመስለብ አርፈው አልተኙም፡፡ሀገራት የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ሀገር እስከ ማፍረስ የደረሰ ኾኗል፡፡ ሊቢያን፤ አፍጋኒስታን፤ የመንና ሶሪያን እንደ ምሳሌ መጥቀስም ይቻላል፡፡
አፍሪካ ላይ የሚነሱ ግጭቶች የኋላ ታሪካቸው ሲታይ ቀላል አይደለም፡፡ በብሔር፤ በጎሳ፤ በወሰን፤ በፖለቲካና በሌሎችም ምክንያቶች ከሚያምጹ አማጺያን ጀርባ የአንዳንድ ምዕራባውያን የተንኮል እጅ አይጠፋም፡፡
ኢትዮጵያ በዋነኛነት ከአንዳንድ ምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ ከገቡ ሀገራት ቀዳሚ ተጠቃሽ ናት፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው የምዕራቡን ዓለም የቀኝ ግዛት እብሪት አስተንፍሳለችና፤ ለመላው አፍሪካ፤ ለመላው የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ምሳሌ ሁናለችና እብሪተኞች ጥርስ ውስጥ መግባቷ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
የታሪክና የሕግ ምሁሩ አልመው ክፍሌ (ዶ/ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ምዕራባውያን “ኢትዮጵያ ላይ ፈረንጅ ተሸነፈ፤ ቀኝ ገዢ ተሸነፈ“ የሚለውን ታሪክ ለመፋቅ እየደከሙ ነው፡፡
የነጻነት ምልክት፤ የአሸናፊነት ምሳሌ የኾነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንቅልፍ የላቸውም ነው ያሉት፡፡
በአሸባሪው ወያኔ የተከፈተው ጦርነት አንዱ ማሳያ ነው የሚሉት ምሁሩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ባላንጣዎች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና ላይ የከፈቱት ጥቃት ነው ብለውታል፡፡ አሸባሪው ወያኔ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ሲነሳ፤ የምዕራባውያንንና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ባላንጣዎችን የውክልና ጦረነት እያስፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተከፈተባትን ጦርነት እየመከተች፤ የምዕራቡን ዓለም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ደግሞ በአደባባይ እየተዋጋች ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአደባባይ የምታደርገው ትግል ዛሬም እንደትላንቱ ምሳሌነት አልቸገረውም ፡፡ “የበቃ ዘመቻ“ን (ኖ ሞር) ስትጀምር መላው አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዘመቻውን በይፋ ተቀላቅለው የእጅ አዙር ቀኝ ግዛትን አውግዘዋል፡፡
በጊዜው ንቅናቄው የበርካቶችን ትኩረት መሳብ ብቻ ሳይኾን ለጊዜውም ቢኾን አደብ ያስገዛ፤ የዘመቻውን ትግል ያነቃቃ ነበር፡፡ ትልቅ የትግል ሜዳ የቲዊተር ዘመቻው የኢትዮጵያዊያን ወዳጆች ርብርብ ሰፊ ነው ፡፡
“ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት ነው እየተዋጋች ያለችው፤ ከኢትዮጵያ ጎን እንቁም“ ያለው ብዙ ነው። በአደባባይ የተካሄዱ ሕዝባዊ ሰልፎች “ዛሬም ኒዎ- ኮሎኒያሊዝምን ለማክሸፍ የሚታክታት ሀገር አይደለችም “ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ለሚቃዡ ሁሉ የተሰነዘረ ቁጣ ነው፡፡ በርካታ መፈክሮች የተሰሙበት ይህ ሰልፍ የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነትና ከሽብር ቡድኑ ወያኔ ጋር የሚያሳዩትን ውግንና አውግዟል፡፡
“ሉዓላዊነታችንና የግዛት አንድነታችንን በጋራ ማስከበራችንን እንቀጥላለን“፤ “የጁንታው ጠበቆች በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሊያቆሙ ይገባል“፤ “የውጪም ኾነ የውስጥ ጠላቶቻችንን መመከት የምንችል ታላቅ ሕዝብ ነን!”…የሚሉ ሃሳቦች የተስተናገዱበት ሕዝባዊ ሰልፍ ነበር የተካሄደው፡፡
“አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረጉት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የትግል ማዕከል ስለኾነች ነው” የሚለው የብዙዎች ሃሳብ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የምዕራባውያን የፖለቲካ፤ የዲፕሎማሲ ጫና የማያንበረክካቸው፤ የወርቃማው የአድዋ ድል የ ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ቤዛ ናቸውና ምሳሌነቱ ዛሬም እንደትላንቱ ይኾናል፡፡
በጋሻው አደመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
