በምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ የገቡት ቀደምት ልዕለ ሀገራት!

228

በዓለም ቀደምት ልዕለ ኃያልና ገናና ከነበሩ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ሮምና ፐርሺያ ግንባር ቀደም ተደርገው ይወሰዳሉ። የቀደምቷ ፐርሺያ አካል የነበሩት (የአሁኑቹ አፍጋኒስታን፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ…) አብዛኛዎቹ በምዕራባውያን ሴራ አንድ በአንድ ፈራርሰዋል። ያ በደማቅ ቀለም የጻፉት ታሪካቸው ዛሬ ላይ ደብዝዟል።

በተለይም ደግሞ የዓለም ልዕለ ኃያል ተደርጋ የምትቆጠረው አሜሪካና አጋሮቿ በቀደምት ገናና ሀገራት ላይ በማነጣጠር ዳግም ታሪካቸው እንዳይነሳ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅና ሶሪያ ደግሞ ገፈት ቀማሽ ከኾኑት ሀገራት መካከል ይገኙበታል።

አኹን ላይ የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ያልተገባ ተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነት ካረፈባቸው ቀደምት ገናና ሀገራት መካከል ደግሞ አንዷ ኢትዮጵያ ናት።

ለመኾኑ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ እያሳዩ የሚገኙት ጣልቃ ገብተትና ሴራ ምክንያት ምንድን ነው?
ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመከፋፈል የሔዱበት የቆየ ሴራ ምን ይመሳላል? የሚሉትን ጉዳዮች ከተለያዩ መጽሐፍትና ያነጋገርናቸው ምሑራን ያነሱትን ሃሳብ አጣቅሰን እናስነብባቹህ።

አንዳንድ ምዕራባውያን ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን በቆንሲል እና በሚሲዮን የሽፋን ስም በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ወደ ፊት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ” የሚያስፈልጋቸውን መረጃዎች ሲሰበሰቡ መቆየታቸውን በላይ ገብረ ጻድቅ “የመረጃና ደኅንነት ሙያ እና የኢትዮጵያ ገጽታው” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።

ከእነዚህ ውስጥም፦

✍️ በ1309 ዓ.ም በፖርቱጋል ንጉሥ ዳግማዊ ዮሐንስ ወደ ኢትዮጵያ ተልከው የመጡ ቀሳውስት መሳይ አሳሾች በሱዳን (በዚያን ጊዜው አጠራር በመረዌ) በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በርካታ ገዳማትን በመጎብኘት ማወቅ የሚፈልጉትን ሁሉ ቃኝተው ተመልሰዋል፡፡

✍️ በ1473 ዓ.ም ብራካሊዮኒ የተባለ ጣሊያናዊ ሰዓሊ ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ ለሠላሳ ሦስት ዓመታት ያህል ቆይታ አድርጎ ነበር። ብራክሊዮኒ ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ተራራና ሸንተረሮች፣ ወንዞችና ፍሰታቸውን በስዕልና በካርታ አስፍሮ ወደ ሀገሩ እንደወሰደ ይነገራል።

እነዚህ መረጃዎች ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ላወጀችው ጦርነት ወታደራዊ ስልትን ለመቀየስ አስፈላጊ መረጃ ሆኖ እንዳገለገለ ይነገራል።

✍️ ጁሴፔ ሳፒቶ የተባለው ጣሊያናዊ ቁጥራቸው በርከት ካለ ሚሲዮናውያን ጋር በመሆን በኤርትራና በቀይ ባሕር አካባቢ ገብቶ በመዘዋወር በቂ መረጃ ሰብስቦ ተመልሷል።

✍️ ፓድሬ ኪርከራ የተባለ ፖርቱጋላዊ የጣናን ሐይቅና አካባቢውን፣ አማኑኤል ዓልሜዳ ዝዋይንና አካባቢውን፣ ፓድሬ በራንስ ደግሞ ትግራይንና አካባቢውን አጥንተው ተመልሰዋል።

✍️ በ1762 ዓ.ም ጀምስ ብሩስ የተባለ የስኮትላንድ ተወላጅ በምፅዋ ወደብ በኩል ገብቶ አሳውርታን፣ አደዋን፣ አክሱምን፣ የተከዜን ዥረት፣ ሰሜን ተራሮችንና የጣና ሐይቅን እየተዘዋወረ አጥንቶ ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1764 ዓ.ም በስናር በኩል ወደ ሀገሩ ተመልሷል።

ብሩስ በእነዚህ አካባቢዎች አድርጎት የነበረው ጂኦግራፊያዊ ጥናት ዓይናቸውን ወደ አካባቢው ጥለው ለነበሩ ቅኝ ገዢዎች አስተዋጽኦ እንደነበረውም ይነገራል።

ጀምስ ብሩስ ኢትዮጵያን ካሰሰ በኋላ በ15 ግመል ሙሉ የተጻፉ መጽሐፍትን መውሰዱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መግለጻውም ይታወሳል።

✍️ በ19ኛው ክፍለ ዘመንም እንግሊዞች፣ ፈረንሳዮች፣ ጣሊያኖችና ሌሎችም አውሮፓውያን በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል ገብተው እየተዘዋወሩ ሰፋፊ ጥናቶችን በማከናወን በቂ መረጃ አጠናቅረው ተመልሰዋል።

✍️ በ1853 ዓ.ም ሙንዚንገር ፓሻ የተባለው የስዊዝ ተወላጅ በኤርትራና ቀይ ባሕር አካባቢ እየተዘዋወረ መረጃ ሰብስቧል። ሙንዚንገር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከነበሩት ሰላዮች መካከል በተለየ ሁኔታ አደገኛ እንደነበር ይነገርለታል። ሙንዚንገር ፓሻ ለሁለተኛ ጊዜ በ1868 ዓ.ም በምፅዋ ወደብ በኩል ገብቶ የእንግሊዝ ጦር ኢትዮጵያን ይወጋ በነበረበት ወቅት ከእንግሊዞች ጋር በመሆን የውጊያው ተካፋይ የነበረ ነው። ሙንዚንገር ለስለላ ሥራው ያመቸው ዘንድ እራሱንና የሚሠራውን ሥራ በመቀያየር ረዘም ላለ ጊዜ ቆይታ አድርጓል። በአንድ ወቅት የፈረንሳይ ወኪል በሌላ ጊዜ ደግሞ የግብፅ እንደራሴ በመሆን በምፅዋ አካባቢ እየተዘዋወረ ጥናቱን ቀጥሏል። ወደኋላውም ግብፆች ኢትዮጵያን ለመውረር ጦር ባዘመቱበት ወቅት ሙንዚንገር 500 ምልምል ወታደሮችን ይዞ በአውሳ በኩል በመዞር አፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት ሲገሰግስ አፋሮች ከበው ከነወታደሮቹ ደምስሰውታል።

✍️ 1835 (እ.አ.አ) አንድ የእንግሊዝ የፓርላማ አባል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የሀገሪቱን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ ሃብት እና የሕዝቡን ሥነልቦና ከተመለከተ በኋላ ሀገሪቱን ማዳከም ካልተቻለ በአፍሪካ ላይ ተሰሚነት እንደማይኖራቸው አቅርበው ነበር፡፡

ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በዘውግ እና በሃይማኖት ወደ ትናንሽ ሀገርነት ከፋፍሎ ለመበታተን ለረጅም ጊዜ ሲሠሩ መቆየታቸውን ታደሰ በቀለ ‹ከቀዳማዊ እስከ ቀዳማዊ› በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረውት ይገኛል።

ለዚህ ደግሞ እንግሊዝ እና ጣሊያን ሀገሪቱን ተሰሚነት የሌላቸው ትናንሽና ደካማ ሀገርነት ለመበታተን የሚያስችላቸውን የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት ለአውሮፓ መንግሥታት አቅርበዋል። እንግሊዞች ኢትዮጵያን ወደ ሦስት ሀገርነት ለመበተን የሚያስችል የጥናት ሐሳብ ለአንዳንድ መንግሥታት አቅርበው “ኤርሳክን” እና “ብሮክስ አርስተን” የተባሉ እንግሊዛውያን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተው እንዲያጠኑ ተደርጓል።

ሴራው በኢትዮጵያ መንግሥት ተደርሶበት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ከሀገር እንዲውጡ ተደርገዋል፡፡ እንግሊዞች በራሳቸው ዜጎች ሳይሳካላቸው የቀረውን ፕሮጀክት ለማሳካት ባንዳዎችን በመጠቀም ያደረጉት ሙከራም ተደርሶበት ሊከሽፍ ችሏል፡፡ እንግሊዞች በዚህ ብቻ ሳያበቁ ‹‹ትግራይ ትግረኛ›› በሚል ትግራይ እና አፋርን ከኤርትራ ጋር ቀላቅለው እንዲገነጠሉ ሙከራ ቢያደርጉም አሁንም በማዕከላዊ መንግሥቱ ተደርሶበት ከሽፏል፡፡

ጣሊያኖችም ሀገሪቱን ወደ ስድስት ሀገራት ለመከፋፈል የሚያስችላቸውን ጥናት አጥንተው የአውሮፓ መንግሥታት እንዲያውቁት እና እውቅና እንዲሰጡት አድርገዋል፡፡ ጥናቱን በ1938 (እ.አ.አ) ‹‹ጊይዶ ዴል አፍሪካ ኦሬንታል ሃሊኖ›› ተብሎ በሚጠራው መጽሐፋቸው ጽሕፈው የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው ቢደረግም ፈረንሳይ እና ኖርዌይ በወቅቱ የኢትዮጵያን መከፋፈል በመቃወማቸው ሴራው ሳይሳካ ቀርቷል።

በቅርቡ ደግሞ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ‹‹ኮማንድ ኤንድ ኮንትሮል ፊውዥን ሴንተር- C2FC – ›› የሚል ስያሜ ያለው ፕሮጀክት ነድፈው እንቅስቃሴ ጀምረው እንደነበር ጅኦፖለቲክስ ፕረስ የተባለ ድርጅት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ምዕራባውያን “ኢትዮጵያን ለመበተን” ምክንያታቸው ምንድን ነው?

ለዚህ ጥያቄ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ጡሬ መኳንንት ከዚህ በፊት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁለት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፣ የራሷ ፊደል እና የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት ከጥንት ገናና ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗ እና የምዕራባውያን ስፔስ ሳይንስ መሰረት በመኾኗ ያ የጥንት ሥልጣኔ ዳግም ማንሰራራት ከቻለ የጥቁር የበላይነትን ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ሁለተኛው በምክንያትነት ያነሱት ደግሞ ኢትዮጵያ የዲኦፖለቲካል አቀማመጧ መካከለኛው ምሥራቅን፣ ቀይ ባሕርን እና አፍሪካን ለመቆጣጠር ስትራቴጅክ ቦታ በመኾኗ ነው።

የአካባቢውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ደግሞ የተጎሳቆለችና የተዳከመች ሀገር በመፍጠር የምዕራባውያንን ጥቅም የሚያስጠብቅ አሻንጉሊት መንግሥት ለማስቀመጥ ሲሠሩ ቆይተዋል።

የግብጽ በቀጣናው ስትራቴጅክ ሀገር ኾኖ መቀጥል በኢትዮጵያ መዳከም ላይ የተመሠረተ በመኾኑ ግብጾችም ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በቀጥታ ኾነ በተዘዋዋሪ ለማፍረስ ሲሠሩ ቆይተዋል።

እነዚህ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የብሔር ልዩነትን እንደ ዋና መሳሪያ አድርገው ሲሠሩ መቆየታቸውን ምሁሩ ገልጸዋል። እንደ አሸባሪው ሕወሓት እና መሰል የውስጥ የታጠቁ ኃይሎችን ሲደግፉም ተስተውሏል። አሸባሪው ሕወሓት ሲመሠረት ጀምሮ በእነዚህ ኃይሎች በእርዳታ ስም ሲደገፍ ቆይቶ አሁንም ዳግም ወደ ነበረበት ለመመለስ ባረጀ እና ባፈጀ የሰብዓዊ እርዳታ የሽፋን ስም ድጋፍ እየተደረገለት መኾኑን ለአብነት አንስተዋል።

የታሪክ ምሁሩ ፤ አሸባሪው ወያኔ በአሁኑ ወቅት የውጭ ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ኾኖ እያገለገለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በአሸባሪው ወያኔ አማካኝነት የተጀመረው ጦርነት በድብቅ የሚሠሩ አካላት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሕልውና ላይ የከፈቱት ጥቃት እንደሆነም የሚታወቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ልማት የማይፈልጉ የረጅም ጊዜ ጠላቶች የሽብር ቡድኑን በጦር መሳሪያ ጭምር በመደገፍ እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ብዙ ደክመዋል፤ ዳሩ ግን አይሳካላቸውም። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ሉዓላዊነት ድርድር አያውቁምና!

በዳግማዊ ተሠራ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼


 

Previous article❝አንበሳውን አስቆጡት፣ የተዳፈነው እሳት አያያዙት❞
Next articleበኩር ጋዜጣ – ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም ዕትም