❝አንበሳውን አስቆጡት፣ የተዳፈነው እሳት አያያዙት❞

332

ጥቅምት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቃት የማይወደውን፣ ጥቃትም የማያውቀውን አንበሳ አስቆጥተውታል፣ ረመጥ አፍኖ የተዳፈነውን እሳት አያያዘውታል፣ ነብሩን ነካክተውታል፡፡ አንበሳው ከተቆጣ፣ እሳቱ ነዲዱን ካወጣ በኋላ የሚያስቆመው የለም፡፡ አትንኩኝ ትላቸዋለች ይነኳታል፣ አትድረሱብኝ ትላለች ይደርሱባታል፣ በክብሬ አትምጡብኝ ትላቸዋለች ይመጡባታል፡፡

አንበሳው ዝም ሲል ጥርሱ ወልቋል ይላሉ፣ እሳቱ ሲዳፈን ጠፍቷል እያሉ ይዘፍናሉ፣ እሳቱ ረመጥ አፍኖ መዳፈኑን፣ አንበሳው ጉልበቱን ይዞ ዝም ማለቱን ግን አያውቁም፡፡ አንበሳውን ይተነኩሱታል አድቅቆ ያስቀራቸዋል፣ የታደፈነውን እሳት ይቆሰቁሱታል ረመጡ ያቃጥላቸዋል፣ አመድ ያደርጋቸዋል፡፡

ገጠሟት መታቻቸው፣ ሞገቷት ረታቻቸው፣ በታች አደረግናት ሲሉ በላይ ታየቻቸው፣ ጨለመች ሲሏት አበራች፣ ደከመች ሲሏት ጎመራች፣ ወደቀች ሲሏት ተነሳች፣ አፈረስናት ሲሉ አጸኗት፣ በተናት ሲሉ የበለጠ አንድ አደረጓት፡፡ እናፍርሳት ያሏትን ታፈርሳቸዋለች፣ እናሳንሳት የሚሉትን ታሳንሳቸዋለች፣ እንበትናት ያሏትን ትበትናቸዋለች፡፡

ቅድመ አያቶቻቸው ተነሱባት ጣለቻቸው፣ አያቶቻቸው ገጠሟት ረታቻቸው፣ አባቶቻቸው መጡባት እንዳልነበር አደረገቻቸው፣ ልጆቻቸው ተተኩ በቁጣ ተነሳችባቸው፡፡ በዘር የሚተላለፍ ሽንፈት አይሰለቻቸውም፣ በዘር የሚወራረስ ውርደት አይበቃቸውም፣ አባቱ በሞተበት ምድር ልጁ ይነሳል፣ ልጁም ይሞታል፡፡

ኢትዮጵያ ማለት ጠላት የማይቀርባት፣ የፈሪ እጅ የማይጨብጣት፣ ጦርነት የማይረታት፣ አሉባልታ የማይፈታት፣ የሚያቃጥሉ ልጆች ያሏት፣ ሽንፈት የማያውቁ አንበሶች የሚጠብቋት፣ ለማሸነፍ ብቻ የተፈጠረች፣ ጠላቶቿን ስትረግጥ፣ ወዳጆቿን ስታጌጥ የኖረች ሀገር ናት፡፡

ገሚሶች በቅናት፣ ገሚሶች በናፍቆት ያዩዋታል፣ በናፍቆት የሚያዩዋት ያከብሯታልና ያገኟታል፣ በምድሯ መጥተው ፍቅርና ደስታ ያዩባታል፣ በቅናት የሚያዩዋት ግን ምድሯን አይረግጧትም፣ ወሰኗን አያልፏትም፡፡ እርሷ ለወዳጆቿ እንጂ ለጠላቶቿ የሚመች ባሕሪ የላትምና፡፡ ጠላቶቿን ታቃጥላቸዋለች፣ እንዳልነበሩ ታደርጋቸዋለች፡፡ ወዳጆቿን ከፍ ከፍ ታደርጋቸዋለች፣ ጀግና የወለደች፣ በጀግኖች የተከበበች፣ በጀግኖች የተመላች ናትና ጠላትን ማዋረድ ወዳጅን መውደድ ታውቅበታለች፡፡

የዓለም ታላላቅ ተቋማት በኢትዮጵያ ዘግተው መከሩ፡፡ እናፍርሳት፣ እናዋርዳት፣ ከፍ ብላ ከተቀመጠችበት የታሪክ መዝገብ ላይ እንሰርዛት አሉ፡፡ ገና በቀደመው ዘመን ጀምረው ተጠራርተው መከሩ፣ ዘከሩ፡፡ ጦር አዘመቱባት፣ የዘመተው ጦር እንኳን ድል ይዞ ሊመለስ ማን ሞተ፣ ማንስ ተረፈ፣ ጦርነቱስ ምን አይነት ነበር ብሎ ወሬ የሚነገር የተመለሰ አልነበረም፡፡ ሁሉም በገባባት ያልቃል፣ ሁሉም በደረሰበት ይቀራል፡፡ ቆይተው ሌላ ምክር መከሩ፣ ከቀደመው የተሻለ የጦር መሳሪያ፣ ከቀደመው የበለጠ ሰራዊት አዘመቱ ያም እንደቀደመው ሁሉ ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ቀረ፡፡ እነርሱ ጦር እንዳዘመቱ እርሷም እንደደመሰሰች ዘመናት ነጎዱ፡፡ ኢትዮጵያዊውን በኢትዮጵያዊነቱ ሲመጡበት ሰይፉ ይቀላል፣ ክንዱ ይጥላል፡፡ ይህ ክፉ ምክራቸው ዛሬም አልቀረም፡፡ በነጩ ቤተ መንግሥት ስለ ኢትዮጵያ ክፉ ይመከራል፣ በአንዳንድ ምዕራባውያን ሰማይ ሥር ስለ ኢትዮጵያ መጥፋት ይዘከራል፡፡ በአፍሪካ ሰማይ ሥር ተከፋይ ባንዳ ይፈለፈላል፡፡

ዓለምን ለጥፋት የምታዘጋጀው፣ በሰላም የሚኖሩ ሕዝቦችን ሀገር አልባ የምታደርገው፣ በአሻገር ጦርነት እየደገሰች ደም የምትጠጣው አሜሪካ ማፍረስ የሚገባትን ሀገራት አፈራርሳለች፣ ባለሀገሮችን ሀገር አልባ አድርጋቸዋለች፣ ባለቤቶችን ቤት አልባ አስቀርታቸዋለች፣ ባለሀብቶችን ፍርፋሪ ለማኝ አድርጋቸዋለች፤ ወንድሙን በወንድሙ ላይ እያስነሳች ምድርን በደም አራጭተዋለች፡፡ ዓለሙን በሰቆቃና በስቃይ ሞልተዋለች፡፡
በሌሎች ሀገራት መፍረስ ላይ ኃያልነቷን የምታረጋግጠው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በሥውርና በግልጽ ከተነሳች ሰነባብታለች፡፡ ኢትዮጵያን ለሚያደሙት፣ ኢትዮጵያን ለሚጠሉት፣ ኢትዮጵያን ለሚወጉት በደም ካካበተችው ካዝናዋ እያወጣች ትለግሳቸዋች፣ አይዟችሁ በሏት፣ ሰላም አትስጧት ትላቸዋለች፡፡

እንደ አሜሪካ ሁሉ በአንዳንድ ምዕራባውያን ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ መጥፋት ይዘምራሉ፣ ታላላቅ ተቋሞቻቸው ስለ ኢትዮጵያ መዳከም ይመክራሉ፡፡ የኢትዮጵያ እውነት፣ ጽናት፣ አይበገሬነት እና ኃያልነት የገባቸው ደግሞ ከእነርሱ በተቃራኒ ቆመው ኢትዮጵያን አትንኩ እያሉ ይከራከራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ጽናት አፍሪካውያን በሙሉ እንደሚጸኑ፣ ኢትዮጵያን ተከትለው አፍሪካውያን በሙሉ እንደሚገሰግሱ ያውቁታልና በኢትዮጵያ ላይ መከራውን ያበዙባታል፡፡ በክብራቸው፣ በሉዓላዊነታቸው፣ በእናት ሀገራቸው እና በኢትዮጵያዊነታቸው ድርድር የማያውቁት ኢትዮጵያውያን ታዲያ በአሻገር የሚደገስባቸውን፣ በአሻገር የሚዶለትባቸውን አይተው ዝም አላሉም፡፡ ተውን አልደረስንባችሁም አትድረሱብንም፣ ለኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን እንበቃታለን፣ ለኢትዮጵያ እኛው ኢትዮጵያውያን እናስባታለን፣ እኛው እንጠብቃታለን አሉ እንጂ፡፡ ባለጊዜዎች ግን ጣልቃ መግባታቸውን አላቆሙም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የተነሱትን አሸባሪዎች ጉድጓድ አውጥተው፣ ነብስ እንዲዘሩ ለማድረግ የሚችሉትን እያደረጉ ነው፡፡

የውጭ ጣልቃ ገብነት የመረራቸው ኢትዮጵያውያን መረረን ብለው ተነስተዋል፡፡ እንደ አንበሳ አግስተዋል፣ እንደ ነብር ተቆጥተዋል፡፡ በቃችሁ፣ ተውን ብለው በአንድነት ወጥተዋል፡፡ አሁን አንበሳው ተቆጥቷል፣ ጥርሱ ስል ነው፣ አሁን የታዳፈነው እሳት ተያይዟል፣ የቀረበውን ሁሉ ያቃጥላል፣

ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ኢትዮጵያዊ እንጂ ባዳ እና ባንዳ አያዝም፣ አይፈርድም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጎዳናዎች በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ አሸብርቀው፣ ኢትዮጵያውያን እልህና ወኔ ታጥቀው ተውን ብለዋል፣ ቁጣቸውን አሳይተዋል፡፡
ʺ ከአባቱ ባድማ የተኛውን በሬ
እየቀሰቀሱ አደረጉት አውሬ ” እንደተባለ አሁን በሀገሩ የመጡበት ሕዝብ ተነስቷል፣ አሁን በክብሩ የተነሱበት ሕዝብ ተቆጥቷል፡፡ ዝም ያለውን አላስቀምጥ ስላሉት፣ በሀገሩ የተቀመጠውን ስለነካኩት ቁጣውን ከልቡ አውጥቶ በአደባባይ አሳይቷል፡፡ ተከፋፍሏል ያሉት ሕዝብ አንድ ኾኖ ታይቷል፡፡ እኩለ ቀን ላይ ቢጨልም፣ መከራው ቢበረክትም ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላይ ድርድር አያውቁም፣ የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ የማንንም ፈቃድ አይጠይቁም፣ በክንዳቸው ክብራቸውን፣ በአንድነታቸው ሀገራቸውን ይጠብቃሉ እንጂ፡፡

ኢትዮጵያን ኢትዮጵያውያን እያሉ ማንም አይነካትም፣ ማንም አይደፍራትም፣ ማንም ከከፍታው ማማ አያወርዳትም፡፡ ተዋት ኢትዮጵያ ከሚታስቡት፣ ከምታቅዱት፣ ከምታልሙት፣ ከምታደርጉት ሁሉ በላይ ናት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼

Previous articleየውጭ ጣልቃ ገብነትንና የአሸባሪውን ወያኔ ወረራ የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
Next articleበምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ የገቡት ቀደምት ልዕለ ሀገራት!