❝ጥበብን ተከተሏት፣ በዙፋኗ ዘውዷን ጭነው ነገሡባት❞

209
ጥቅምት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ ሰዎች አሉ ለጥበብ የኖሩ፣ በጥበብ ያደሩ፣ በጥበብ ፍቅር የታሰሩ፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሉ በመልካሙ ጎዳና የሚሮጡ፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ ከማያረጅ ዙፋን ላይ የማይወልቅ ዘውድ ጭነው የሚቀመጡ፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ ጥበብ የወደደቻቸው፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ ጥበብ ያነገሠቻቸው፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ ጥበብ የጠበቀቻቸው፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ ጥበብ ሞሽራ ያኖረቻቸው፡፡
ጥበብን ተከተሏት፣ አፈቀሯት፣ አትክጅኝ አልከዳሽም አሏት፣ እርሷም ሳትከዳቸው፣ እርሳቸውም ሳይከዷት፣ እንዳከበሯትና እንደ ወደዷት ዘመናቸውን ፈጸሙ፡፡ የሰው ልጅ ግብር ኾነና በስጋ አለፉ እንጂ ታሪካቸውስ በትውልድ ልቦና ተቀርጾ ይኖራል፣ ጥበባቸውስ በዓለሙ ሁሉ ያበራል፣ ስማቸውስ ከመቃብር በላይ ኾኖ ታላቅነታቸውን ይመሰክራል፡፡
ጥበብን በልጅነት ዘመናቸው አስበዋታል፣ በወጣትነት ዘመናቸው ኑረውባታል፣ በእርጅና ዘመናቸው ምርኩዛቸው አድርገዋታል፡፡
ነገሥታቱ አያሌ ታሪክ የሠሩባት፣ ሃይማኖት የጸናባት፣ የኢትዮጵያ ስም ከፍ ከፍ ብሎ የሚጠራባት፣ አንድነት የሚሰበክባት ስመ ጥሯ ከተማ ተሞሽራለች፡፡ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ነገሥታቱ፣ ሊቃውንቱ፣ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች ከትመውባታል፣ ስለ ሀገር አንድነት መክረውባታል፡፡ ረዘም ያለ እድሜ ያላት ያቺ ከተማ በስመ ገናናው ንጉሥ ዘመን አብዝታ ገነነች፡፡ ስመ ገናናው ንጉሥ ምኒልክ ቤተመንግሥታቸውን አንጸውባታል፣ በጥበብ እና በግርማ ኖረውባታልና፡፡
ይህች ከተማ የዙፋን መቀመጫ፣ የነገሥታቱ መኖሪያ ኾና ኖራለች፡፡ አባ ዳኛው አልፈው፣ ልጅ ኢያሱና ዘውዲቱ ተተካክተው፣ ዘመኑ ተከታትሎ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ደርሶ ነበር፡፡ እሳቸው በአባቶቻቸው ዙፋን ላይ ተቀምጠው ሀገር ያስተዳድሩ ጀምረዋል፡፡ አስቀድመው የቤተ መንግሥቱን ጥበብ የተካኑት ግርማዊነታቸው በዙፋኑ ላይ ተደላድለውበታል፡፡
የሸዋ ካህናት ዋዜማ ቆመዋል፡፡ በነገሥታቱ መቀመጫ አንኮበር የሚኖሩ የበዙ ካህናት በታላቁ ደብር ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ማኅሌቱን አድምቀውታል፡፡ በቤተ መቅደሱ በየደረጃቸው የተሰደሩት ካህናት እርሳቸው መዝሙሩን ይበሉት፣ አይ እሳቸው ይሻላሉ፣ እርሳቸው ቅኔውን ይቀኙት፣ አይ በእርሳቸው ያምራል እየተባባሉ በፍጹም ትሕትና ሲያመሰግኑ አድረዋል፡፡
ዘመኑ ጥቅምት 12/1925 ዓ.ም ነበር፡፡ ያቺ የሸዋ ነገሥታት መቀመጫ አንኮበር መቼም ለታሪክ ተፈጥራለችና አንድ ታላቅ ሰው እትብታቸው ይቀበርባት ዘንድ ተመርጣለች፡፡ ለከፍታ መዘጋጀት ጥሩ ነውና በጉያዋ ተገኝተው ሀገርን ከፍ የሚያደርጉ ብላቴና ሊመጡ ነው፡፡
በታላቁ ደብር ጽሕናጽሕኑ ሲንሿሿ፣ ከበሮው ሲመታ፣ ካህናቱ ሲያረግዱ አድረዋል፡፡ የመላኩ ሚካኤል ወርኃዊ በዓል የሚከበርበት ነውና ምሥጋናው ከፍ ከፍ ብሏል፡፡ እልልታው ደምቋል፡፡ ካህናት እና ዲያቆናት ምድራዊ መላእክት መስለዋል፣ ፈጣሪ ምሥጋናቸውን ይቀበላቸው፣ ሀገራቸውን ይባርክላቸው፣ በረከትና ረድኤት ይሰጣቸው ዘንድ ያለ ማቋረጥ ምሥጋና ላይ ናቸው፡፡ ሊቃውንቱ እንዲህ በሚያረግዱበት፣ ምድራዊ ሳይኾን ሰማያዊ በሚመስል ሥርዓት በተዋቡበት በዚያ ጊዜ በነገሥታቱ ከተማ የሚኖሩ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው አንዲት እናት ምጥ ተይዘው ነበር፡፡ ሊቃውንቱ በቅዱስ ሚካኤል አጸድ ሥር ወደ ፈጣሪያቸው ምሥጋና ያቀርባሉ፣ መልካሟ እናት ደግሞ በቤታቸው ልጃቸውን በሰላም ይገላለገሉ ዘንድ በጭንቀት ይማጸናሉ፡፡
ለዘጠኝ ወራት በማሕጸን የተሸከሙት ልጅ ምድርን ሊጎበኛት መንገድ ጀምሯል፡፡ የልጃቸውን ዓይን ለማየት ቢቻኮሉም ምጡ ግን አስቸግሯቸዋል፡፡ ሌሊቱ ነግቷል፣ ምዕመናን ከወርኃዊ ከቅዱስ ሚካኤል በዓል በረከት ለመሳተፍ በአጸዱ ዙሪያ ተኮልኩለዋል፣ ካህናቱ ሲያመሰግኑ አድረው በምሥጋናቸው ቀጥለዋል፡፡ ምጥ የተያዙት እናት የሚወዱት መላእክ በሚከብርበት ዕለት የተወደደ ወንድ ልጅ ተሰጣቸው፡፡
ወር በገባ በአሥራ ሁለተኛው ቀን የተወለደው ልጅ እልል ተባለለት፣ ከአስጨናቂ ምጥ በኋላ ቤቱ በእልልታና በደስታ ተመላ፡፡ ያማረ ደም ግባት ያለው ልጅ ተሰጥተዋልና እናት እና አባቱ ስም ሲያወጡ አፈወርቅ አሉ፡፡ ወርቅ የኾነ ስም፣ ወርቅ የኾነ ልጅ፣ ወርቅ የኾነ ቀን፣ ወርቅ የኾነ ምድር፡፡
አባቱ ተክሌ ማሞ፣ እናቱ ደግሞ ፈለቀች የማታወርቅ ይባላሉ፡፡ ልጃቸው አፈወርቅ ተክሌ ይሰኛሉ። ሃይማኖታቸውን የሚያከብሩ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ በቀዬውም የተከበሩና የተወደዱ ደጋግ ጥንዶች ነበሩ፡፡ አፈወርቅ በተወለዱበት በዚያ ዘመን ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ወረራ ልትሞክር እያከቦበኮበች ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የዓድዋው ዘመን ይበቃል ተይኝ እያለች ነው፡፡ ኢጣሊያ ለጦርነት አብዝታ ተዘጋጄች፡፡ በ1928 ዓ.ም ወረራ ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያውያንም በጀግንነት ከወራሪዎች ጋር ይዋደቁ ጀመር፡፡ ጦርነቱ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ኾነ፡፡ ጣሊያኖች እንወራለን፣ ኢትዮጵያውያን አንወረርም፣ ጣሊያኖች እናስገብራለን ኢትዮጵያውያን አንገብርም የመረረ ጦርነት ተካሄደ፡፡ ዳሩ እንደ ዓድዋው ዘመን በአጠረ ቀን ድል አልተገኘም፡፡ ጀግኖቹ በዱር በገደል ለሀገራቸው ይዋደቁ ነበር፡፡ በዚሕ ዘመን ብላቴናው አፈወርቅ ገና ከእናታቸው ጉያ አልወጡም ነበር፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ ታሪካዊ በኾኑ ሥፍራዎች የሚያደርሱት ግፍና በደል ላቅ ያለ ነበር፡፡
በዓድዋ ተራራ ላይ አንገት ባስደፏቸው ንጉሥ መናገሻ ሥፍራ አንኮበር ሲደርሱ ንጉሡን ያገኟቸው ይመስል የከፋ በደል አደረሱ፡፡ ይህን በደላቸውንም ብላቴናው አፈወርቅ በልጅነት እድሜያቸው አዩ፣ ተመለከቱ፡፡ ድል ለኢትዮጵያ የተገባች ነበረችና ኢጣሊያ ደግም ተቀጥቅጣ ከኢትዮጵያ ተባረረች፡፡ ይህን ጀግንነት ብላቴናው አፈወርቅ ተመለከቱ፡፡
ብላቴናው አፈወርቅ በዚያው በለጋ እድሜያቸው ፊደል ቆጠሩ፣ ጥበብን መረመሩ፡፡ ገና በለጋ እድሜያቸው በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ለንደን ተጓዙ፡፡ በለንደንም የሥነ ጥበብ ተቋም ትምህርታቸውን ተከታተሉ፡፡ ወደ ፓሪስም ተሻገሩ፡፡ በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና በሮም የቫቲካን ቤተ መዘክር በሚገኙ የኢትዮጵያ የብራና ሥዕላዊ ጽሑፎች ላይ የረቀቀ ጥናት አደረጉ፡፡
በሥዕል፣ በቅርጻቅርጽና በሥነ ሕንጻ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ የመጀመሪያ የተባለለትን የሥዕል አውደ ርዕይም በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ አሳዩ፡፡ ባሳዩት ነገርም እፁብ ድንቅ ተሰኙ፡፡ የአራዳው ጊዮርጊስን በረቀቀ ሥዕል አንቆጠቆጡት፡፡ እጣቶቻቸው ሥዕል ያሳምራሉ፣ ዓይኖቻቸው መልካም ጥበብ ያያሉ፣ ጀሮዎቻቸው መልካም ነገር ይሰማሉ፣ ስለ መልካም ነገር ያስባሉ፡፡
ʺየእኔ አተያይ የተመሠረተው በአያት ቅድመ አያቶቼ ቅመም ነው፡፡ እርሱን ነው ያጎለበትኩት” ይላሉ ታላቁ የጥበብ ሰው፡፡
ያለ እረፍት አሰቡ፣ አብዝተው ተጠበቡ፣ ቀለማትን አሰባሰቡ፣ ዙሪያ ገባውን አስዋቡ፡፡ እርሳቸውን ማን ይረሳቸዋል ማንስ ይዘነጋቸዋል፣ʺተራራዎችና የጣሪያው ሰማይ ደመና የሚታዪት ሰገነት ላይ ስወጣ ነው” ይላሉ በተወለዱበት የአንኮበር ቤተ መንግሥት ወደ ሰገነቱ ሲወጡ፡፡ ከሰገነት ጋር የተለየ ፍቅር አላቸው፡፡ በእርሳቸው እጣቶች የማይሞሸር፣ በእርሳቸው ጥበብ የማያምር የለም፡፡ አተኩረው ያዩታል፣ አይተው ይስሉታል፣ ስለው ያሳምሩታል፡፡ ትናንትን በሥዕላቸው ያስታውሳሉ፣ በሥዕሎቻቸው ታሪክ ይዘክራሉ፣ በሥዕሎቻቸው ዛሬን ይመዘግባሉ፣ ነገን በትንቢት ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ጀግኖች፣ የኢትዮጵያን የተዋቡ ሥፍራዎች በሥዕሎቻቸው አስውበው አስቀመጧቸው፡፡ በተካኑበት ጥበብ ስማቸው ከፍ ብሎ ተጠርቷል፡፡
ዝም ብለው አይጠሩም፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እየተባሉ ይጠራሉ እንጂ፡፡ ይህ የከበረ ስም ዝም ብሎ የተሰጣቸው አይደለም፤ ባሳዩት የረቀቀ ጥበብ በዓለም አደባባይ ልቀው በመገኘታቸው ነው እንጂ፡፡ የረጅም ጊዜ ጓደኛቸው የነበሩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሲገልጹ ʺለንደን በነበሩበት ጊዜ ወደ አንድ ታክሲ ሊገቡ ሲሉ አንዲት ሴት አየቻቸውና ከሰው በላይ ሰው አለቻቸው፡፡ እውነትም ከሰው በላይ ሰው” ይላሉ፡፡
ሥዕሎቻቸው ዝም ብለው ሥዕል አይደሉም፡፡ ከላይ የሚታይ ድንቅ ውበት አላቸው፣ ተመስጦን የሚጠይቅ፣ የረቀቀ ማሰብን የሚሻ ምስጢር አላቸው፣ በሥዕሎቻቸው ውስጥ የበዙ ጥበቦች እና ምስጢሮች ሞልተዋል፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ʺበኢትዮጵያ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስማ ክፉ አትናገር” ይላሉ፡፡ ይህ ሁልጊዜም ከአንደበታቸው የማይወጣ መርሃቸው ነው ይሏቸዋል፡፡ ʺበዓለማችን ላይ ምርጦች አሉ፤ ደግሞም የምርጦች ምርጥ አለ፣ እርስዎ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰው የሚለውን ስም ተጎናጽፈዋል፣ የአሜሪካ ባዮሎጂካል ኢንስቲትዩት ላበረከቱት ድንቅ የጥበብ ሥራ የበዛ አድናቆቶቱን ይገልጻል” እንዲህ የተባሉት በአሜሪካ በተካሄደ አንድ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ በዚህም ሥነ ሥርዓት ከበዙ ሰዎች መካከል ተመርጠው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የታላቅ አዕምሮ ባለቤት ተብለው ተሸለሙ፡፡
ʺኢትዮጵያ ምን ሠራህ? ብላ ትጠይቀኛለች” የሚሉት ታላቁ ሰው ሀገራቸው ለምትጠይቃቸው መልስ ይኾን ዘንድ ዘመናቸውን ሀገራቸውን ከፍ ከፍ በሚያደርግ ሥራ ተጠመዱ፡፡ በዓለም አደባባይ ከፍ ከፍ እያሉ በሽልማት ተንበሸበሹ፡፡ ኢትዮጵያን በረቀቀ ጥበባቸው አስጠሯት፣ ቀዳሚም አደረጓት፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስማቸውና የሕይዎት ታሪካቸው ከሀገራቸው ሰንደቅ ጋር ከምድር አልፎ ወደ ጨረቃ ከተላከላቸው የከበሩ ሰዎች መካከል አንደኛው ናቸው፡፡
የነገሡባት ጥበብ ዛሬም እንዳነገሰቻቸው ነው፡፡ ለምን እርሳቸው እጅግ የተከበሩ ጥበበኛ ናቸውና፡፡ ታላቁ ሰው ምድርን የተቀላቀሏት ልክ በዛሬዋ ቀን አንኮበር ላይ ነበር፡፡ ስለ ረቀቁት የጥበብ ሥራዎችዎ እናመሰግንዎታለን፣ በረቀቁት ሥራዎችዎ እንማርበታለን፣ ዘመን ስለማይሽረው ሥራዎ ክብር አንሰጣለን፣ ስምዎትን እያነሳን እንዘክራለን፡፡ መልካም ልደት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous article“ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ በሰላም ተጠናቅቋል” የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት
Next articleየውጭ ጣልቃ ገብነትንና የአሸባሪውን ወያኔ ወረራ የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።