
አዲስ አበባ:ጥቅምት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የከተማ አሥተዳደሩ ሕዝባዊ ሰልፉን በተመለከተ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ሕዝብ ዛሬ ከጫፍ ጫፍ በመነሳት “ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን እቆማለሁ፤ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ደማቅ በሆነ መንገድ ተካሂዶ መልእክቱን እጅግ ጉልህ እና ግልፅ በሆነ መንገድ ለመላው ዓለም በማስተላለፍ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጠናቋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በእርግጥም ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ነን። ሰላም ወዳድነታችን እና ለሰላም ዘብ መቆማችንን በተደጋጋሚ በተግባር ያረጋገጥን ሕዝቦች ነን።
ነገር ግን በሉዓላዊነታችን እና በግዛት አንድነታችን ከመጡብን ደግሞ በአብሮነት እና በኅብረት ቆመን ሀገራችንን የምንከላከል፣ ለሀገራችን አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት የምንከፍል፣ ኢትዮጵያን በውድ የደም እና የአጥንት ዋጋ ያሸጋገርን ወደፊትም የምናሸጋገር ፅኑዕ እና ሀገር ወዳድ ሕዝቦችም ጭምር ነን።
ዛሬም ይህ ሀገር ወዳድነት በከተማችን መስቀል አደባባይ ተረጋግጧል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማችን ነዋሪ “የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል” በማለት ከየአቅጣጫው በመጉረፍ የፖለቲካ አመለካከት፣ ብሔር፣ የእምነት ልዩነት ሳይኖር በአንድነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ በማሰማት ሕዝባችን ሰላማዊ እና ሀገር ወዳድ መሆኑን ለጠላትም ለወዳጅም በማያወላዳ መልኩ ማሳየት ችሏል።
የከተማችን ነዋሪዎች በነቂስ በተሳተፉበት በዚህ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጎልቶ በታየበት የሰላማዊ ሰልፍ ወጣቶች፣ ሴቶች ጎልማሶች፤ እናቶች እና አባቶች፤ አካል ጉዳተኞች፤ መምህራን፤ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፤ የግል ድርጅት ሠራተኞች፣ አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም አባት አርበኞች በአጠቃላይ ከሁሉም ዓይነት የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የከተማችን ነዋሪዎች ገና ከሌሊት ጀምሮ በነቂስ በድቅድቅ ጨለማ ገንፍሎ በወጣ ሀገር ፍቅር ስሜት በመውጣት በየመንገዱ ድምጻቸውን እያሰሙ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል።
ለዚህም መላውን ሰላም ወዳድ እና የሰላም አምድ የሆነው የከተማችንን ነዋሪ፤ የፀጥታ ኃይል እንዲሁም ይህ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ያስተባበራችሁ እና ያቀናጃችሁ የሲቪክ ማኅበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና አባላት በተጨማሪም በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች የከተማ አሥተዳደራችን ስላበረከታችሁት ታላቅ አስተዋጽኦ ምሥጋናውን ያቀርባል።
አሁንም ቢሆን የጀመርነውን ሀገራችንን ከጠላት የመጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጠል፤ ለመከላከያ ሰራዊታችን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንድንቀጥል እያሳሰብን በየአካባቢው ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ጠላቶቻችን ቅጥረኞችን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር በመከላከል እና አጋልጠን በመስጠት ዘላቂ ሰላማችንን እናድናረጋግጥ አደራ ለማለት እንወዳለን።
በመጨረሻም የጀመርነው የሀገራችንን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች በማስቀጠል ዋነኛው የሉዓላዊነት ምንጭ ራስን በመቻል ከጥገኝነት በመላቀቅ የሀገርን ብልጽግና ማረጋገጥ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን በደም የተገነባችዋን ሀገራችንን በላባችን ከፍ በማድረግ የኢትዮጵን ብሎም የከተማችንን ብልጽግና እውን እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ አብሮነት እና ኅብረት ታፍራ እና ተከብራ ትኖራለች!!
ጥቅምት 12/ 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
