
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም እና የኢትዮጵያን እውነት የሚደግፍ ሰልፍ ጥቅምት 13/2015 ዓ.ም ሊካሄድ መኾኑን የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገልጸዋል።
አቶ ግዛቸው የውጭ ተላላኪዎች በኢትዮጵያ ላይ እነሱ የሚዘውሩት አይነት መንግስት ለመፍጠር ጣልቃ እየገቡ መቆየታቸውን አንስተዋል። ይህንን ለመቋቋምም በሀገር
ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን እውነት በማስረዳት ሲታገሉ ቆይተዋል ብለዋል።
አሁንም ቢኾን በውጭ ሀገራት የድጋፍ ሰልፎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲኾን በሀገር ውስጥም ጥቅምት 13/2015 ዓ.ም የድጋፍ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የድጋፍ ሰልፉ በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና በመሳሰሉት ትልልቅ የክልሉ ከተሞች እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።
መንግስት ለሰልፉ ፈቃድ የሰጠ ሲኾን በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ የፀጥታ ሥራ ይከናወናል ብለዋል። ሕዝቡም በሰልፉ ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከጠላት አጀንዳ ራሱን በጠበቀ መልኩ መሳተፍ እንዳለበት አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!