
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የትግራይ ክልል ሕዝብ ለዓመታት ግፍ እየፈጸሙበት ያሉትን የአሸባሪው ወያኔ አመራሮች ለፍርድ ማቅረብ እንዳለበት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ሕዝቡ በአንዳንድ የውጭ ኃይሎችና በሽብር ቡድኑ መሪዎች ሴራ ሲፈጸምበት የኖረው ግፍ የሚያበቃበት ጊዜ መቃረቡን መገንዘብ ይገባዋል ብለዋል።
ዶክተር አረጋዊ ለኢዜአ እንደገለጹት የወያኔ የሽብር ቡድን በሀገሪቱ ለውጥ ከተመዘገበ ወዲህ የተሰጠውን የሰላም እድል ባለመጠቀም የትግራይን ክልል ሕዝብ በውስጡ ተሸሽጎ ለስቃይ ዳርጎታል።
የሽብር ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ የዘረጋው የጥቅም ትስስር ተጋሪ የሆኑ የውጭ ኃይሎችና ዳያስፖራ ደጋፊዎቹ አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ አንድም ቀን ኮንነውት አያውቁም ነው ያሉት።
ከዚህ ይልቅ የሽብር ቡድኑን እንደገና ወደ ስልጣን ለመመለስና የጥቅም ተጋሪነታቸውን ለማስቀጠል አልመው በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስ።
በዚህም የሽብር ቡድኑ የትግራይን ክልል ወጣቶችና ህጻናት ለጦርነት በማሰለፍ የፈጸማቸውን የጦር ወንጀሎች እንዳልተፈጸሙ በመካድ ከእውነት ጎን አለመቆማቸውን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል ብለዋል።
የትግራይ ክልል ሕዝብም በሽብር ቡድኑ የጭቆና ስርዓት ምክንያት ብዙ ግፍ እየደረሰበት ሲሆን ወጣቶችም ፊታቸውን ወደ ልማት እንዳያዞሩ ተገድደዋል ነው ያሉት።
ዶ/ር አረጋዊ አክለውም የትግራይ ክልል ሕዝብም ይሔንን ሴራ ሊቃወም የሚችልበት እድል እየተከፈተ መሆኑን መገንዘብ እንዳለበት አመላክተዋል።
የሸብር ቡድኑ መሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የትግራይ ህዝብ ከፍትኛ ሚና መጫወት እንዳለበት ነው የጠቆሙት። የሽብር ቡድኑንና የጥቅም ተጋሪ የውጭ ኃይሎችን ሴራ መቃወም እንደሚገባ ተናገረዋል።
በነገው ዕለት “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ!” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ መግለጹ ይታወሳል።
ሰልፉን የአዲስ አበባ የተፎካካሪ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት፣ የሙያ ማህበራት እና የሲቪክ ማህበራት በጋራ ማዘጋጀታቸው ተመላክቷል።
የሰልፉ ዓላማ የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ፣ የአንዳንድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማውገዝ እና ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ሀገራትን ማመስገን መሆኑም ተነግሯል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!