
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለምን የሚዘዉሩ ሀገራት በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ልዕልና ላይ የደረሱት መኾናቸው እሙን ነው። መታፈር፣ መከበርም ኾነ መደመጥ የሚቻለው እራስን ጠንካራ አድርጎ መሥራት በሚቻልበት ልክ መኾኑ እርግጥ ነው።
ስንዴ እየመጸወቱ “ካለእኛ ቸርነት አትኖሩም” ማለት የሚዳዳቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በሌላው ሀገር ሉዓላዊነት ጣልቃ እየገቡ የሚፈተፍቱትን መታዘብ በቂ ማሳያ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ሰሞኑን ለወጣቶቹ ባስተላለፉት ምልዕክት በኢኮኖሚ እራስን መቻል እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል። ሃሳብ፣ እወቀት፣ ጉልበት እና በቂ ቁጥር ያለው ወጣት እያለ፣ በተፈጥሮ የታደለች ሀብት ያላት ሀገር ይዞ በድህነት መቆዘም ማብቃት አለበት ነው ያሉት።
ርእሰ መስተዳደሩ እንዳሉት ሀገሩን የሚወድ እራሱን ያስከብራል፣ ለሀገሩ ሉዓላዊነት፣ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነትና ነፃነት ይታገላል።
ወጣቶች ለሀገራቸው ክብር በኢኮኖሚውም ዘርፍ ጠንካራ መኾን እንዳለባቸውም ነው ርእሰ መሥተዳደሩ የመከሩት።
“ህልውናችን፣ ሉዓላዊነታችን በደማችን እንደምናስከብር ኹሉ በላባችን ሠርተን ድኅነትን ማስወገድ ያስፈልጋል” ነው ያሉት። በኢኮኖሚ ጥገኛ የኾች ሀገር፣ በኑሮው ተመጽዋች የኾነ ሕዝብ ይዞ የሀገርን ሉዓላዊነት ማሰከበር፣ ሰላምና ደኅንነትን በሚገባ ማረጋገጥ ፈታኝ ነው ባይናቸው።
በአማራ ክልል ከግብርናው እስከ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተስፋ ሰጭ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ነው የተናገሩት ርእሰ መሥተዳደሩ። ሁሉም በየዘርፉ በተሰማራበት የሥራ መስክ ተግቶ መሥራት ጦርነቱን መሸከም እና በሁኔታዎች ወድቆ የማይቀር ኢኮኖሚ መገንባት በዘላቂነት የሚታሰብበት ጉዳይ ነው መኾኑን አብራርተዋል።
ርእሰ መስተዳደሩ እንዳሉት እውቀትና ጉልበት ያለው ነገር ግን የሥራ እድል ያልተፈጠረለትን ወጣት ታሳቢ ያደረጉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራት የጊዜው መፍትሔ የሚሻ ተግባር ኾኗል።
በክልሉ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መኾኑን የጠቆሙት ርእሰ መሥተዳደሩ በየቅጥር ማስታወቂያ ቦርዱ የሚባዝነው ሥራ ፈላጊ፣ በየተቋማት በሚወጣ ክፍት የሥራ ቦታ ለመግባት የሚመዘገብና የሚወዳደር እልፍ ቁጥር ያለው የሰው ኀይልን መታዘብ በቂ ነው።
የክልሉ ሥራና ስልጠና ቢሮ በበኩሉ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ቢጨምርም የሥራ እድል ፈጠራውም በዛው ልክ እያደገ መኾኑን ጠቁሟል።
በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያው የሩብ ዓመት ስለተከናወኑ የሥራ እድል ፈጠራ ሥራዎች ሁኔታን በተመለከተ ከአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ጋርም ቆይታ አድርገናል።
ምክትል ቢሮው ኀላፊው አወቀ ዘመኑ እንደተናገሩት በ2015 ዓ.ም ለ1ሚሊዮን 203 ሺህ 180 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን አስረድተዋል። በዚህም 794 ሺህ 538 ሥራ ፈላጊዎችን መመዝገባቸውን ነው የተናገሩት። ከተመዘገቡትም ቁጥራቸው 118 ሺህ 217 የሚኾኑት ሥራ ፈላጊዎች የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ምሩቃን መኾናቸውንም ምክትል ኀላፊው ጠቁመዋል።
አቶ አወቀ እንዳሉት ባለፉት ሦስት ወራት የእቅዱን 15 በመቶ ለማሳካት ለ180ሺህ 477 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታልሞ በተሠራው ሥራ ለ129 ሺህ 865 ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር የእቅዱን 72 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው ባደረጉት ንግግር የሥራ እድል ፈጠራው የተከናወነው በግብርና፣ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች መኾናቸውን አብራርተዋል።
በሩብ ዓመቱ በኢንዱስትሪና ማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ብቻ 70 ሺህ 194 ሰዎችን፣ በግብርናው ዘርፍ ድግሞ 37 ሺህ 181 ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ጋር ማገኛኘት ተችሏል ብለዋል።
የሥራ እድል ፈጠራው በቅጥርና በኢንተርፕራይዝ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ የሚሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ነባር ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከርም ለሌሎችም በቅጥር የሥራ እድል እንዲፈጥሩ እየተደረገም ስለመኾኑ ነው የተናገሩት።
በየከተሞቹ በርካታ የሥራ ፈላጊዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሼዶችም በስርዓት እንዲመሩና ወጣቶች ሠርተው እንዲለወጡባቸው እየተሠራ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
በቀጥታ ድጋፍ በአዲስ ኢንተርፕራይዝ በማቋቋም ለ52 ሺህ 825 ሥራ ፈላጊዎች ወደ ሥራ መቀላቀላቸውንም አንስተዋል። ነባር ኢንትርፕራይዞችን በማጠናከርም 25 ሺህ 990 ሥራ ፈላጊዎችን እንዲቀጥሩ ማድረግ እንደተቻለም አቶ አወቀ አስረድተዋል።
ቀሪዎቹ በልማት ድርጅቶችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተቀጠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በቀሪው በጀት ዓመቱም የሥራ እድል ፈጠራ እቅዱን ለማሳካት በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!