አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም- የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

192
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የበርካታ ሕዝብ መኖሪያ እና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነችውን አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ አሁንም የቅኝ ግዛት ስሜቱ እንዳለ ማሳያ መሆኑን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጸዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ከ15 የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል።
የአፍሪካና የእስያ ሀገራት በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራቸው መደረጉ ፍትሐዊነት የጎደለው እና ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
በርካታ የሕዝብ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሀብት እና ለዓለም ኢኮኖሚ የጎላ አበርክቶ ያላት አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ኖሯት የራሷን ድምፅ ማሰማት የምትችልበት ዕድል መኖር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
አፍሪካ የራሷ ጉዳዮች ውሳኔ በሚሰጥበት ታላቅ መድረክ ላይ የዳር ተመልካች መሆኗ በፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ ላይ አሁንም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እንዳለ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ሩሲያ “አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል” የሚል ፅኑ አቋም እንዳላትም ነው የገለጹት ቃል-አቀባይዋ።
በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ከሚከሰቱ ግጭቶች አብዛኛው ቅኝ ገዥዎች ትተውት ባለፉት የጠብ እና ግጭት ምክንያቶች መሆኑንም አብራርተዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ የሚከሰቱ ችግሮችን አፍሪካዊያን በራሳቸው የመፍታት አቅም ስላላቸው ይኸው ነፃነታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ብለዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው፤ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካዊያንን ጉዳዮች በራሱ አቅም እና በነጻነት መፍታት የሚችል ተቋም መሆኑን ሩሲያ ታምናለች ብለዋል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ከተሞች ከአላማጣ ሰብስቴሽን ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ጥገና ሊጀመር ነው
Next articleአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መንግሥት በአፍሪካ ህብረት በኩል በሚካሄደው የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አስታወቁ።