
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ከተሞች እና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ከአላማጣ ሰብስቴሽን በመሆኑ የጥገና ሥራው በቅርቡ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ገልጸዋል።
የጥገና ሠራተኞቹ ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉበት ሁኔታ በአሁን ጊዜ የተፈጠረ በመሆኑ በቅርቡም ጥገናው እንደሚጀመር ኃላፊው ለኢብኮ አረጋግጠዋል።
በሰሜን ወሎ እና ዋግኸምራ አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አጥረት ሲያጋጥም ወራት ማስቆጠሩ ይታወቃል።
አቶ ሞገስ መኮንን በሰሜን ወሎ እና ዋግኸምራ ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም ሥራ ለማስጀመር እቅድ ወጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም፣ እንደ ቆቦ እና ላሊበላ ያሉ አካባቢዎች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በዋናነት ሰሜን ወሎ የሚገኙ ከተሞች እና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ከአላማጣ ሰብስቴሽን መሆኑን ጠቅሰው ሰራተኞቹ ስራቸውን ማከናወን የሚችሉበት ሁኔታ በአሁን ጊዜ የተፈጠረ ሲሆን በቅርቡም ጥገና እንደሚጀመር ኃላፊው ተናግረዋል።
የአካባቢው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታሮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከጦርነቱ ማግስት ተጠግነው ወደ ስራ መግባታቸውን እና አሁን ውድመት በመድረሱ ዳግም ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በላሊበላ፣ ዋግኸምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ያገኙበት የነበረው ሰብስቴሽን በአሸባሪው ወያኔ ታጣቂዎች ተነቅሎ መወሰዱ ይታወሳል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
