በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ነገር የለም – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

161
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር በታቀደው መሰረት እየሄደ ነው” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
መንግስት የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ውይይቱ የሚካሄድበትን ቀን እስኪያሳውቅ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
“አንዳንዶች በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል በሚል እየተጠቀሙበት ያለው አገላለጽ ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
“ግጭቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ነበር አሁን ያ ነገር የለም፤ የመከላከል እርምጃው በታሰበው መልኩ እየሄደ ይገኛል” ነው ያሉት።
የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትና አገልግሎትን እንደሚጀመር ነው አምባሳደር ሁሴን በመልዕክታቸው የጠቆሙት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ትናንት በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” በሚል ከእውነታ የራቀ አስተያየት መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ባወጣው መግለጫ መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር በትግራይ ክልል የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የፌዴራል ተቋማትንና ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን የግድ ለመጠበቅ እንደሚገደድ መግለጹ ይታወሳል።
ከዚህም ባሻገር በመንግሥት ቁጥጥር ስር በሆኑ አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ በተሻለ መንገድ መቅረብ እንዲችልና የእርዳታ ሠራተኞች ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን መንግሥት ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous articleአሸባሪው ወያኔ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሚላከውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለራሱ በመጠቀም ለሕዝብ ያለውን ግዴለሽነት አሳይቷል ሲሉ አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) ተናገሩ፡፡
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ከተሞች ከአላማጣ ሰብስቴሽን ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ጥገና ሊጀመር ነው