
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ወያኔ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሚላከውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለራሱ ጥቅም በማዋል ለሕዝብ ያለውን ግዴለሽነት በተግባር ማሳየቱን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ-መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ህዝብ ላይ በደል የሚፈጽመው አሸባሪው ወያኔ ፤ በትግራይ ክልል ሕዝብ ትከሻ ላይ ተጭኖ የከፋ በደል መፈጸሙን ቀጥሎበታል ብለዋል።
ወደ ክልሉ የሚላከውን ሰብዓዊ ድጋፍ በመዝረፍ ሕዝቡን ለችግርና ሰቆቃ መዳረጉን ቀጥሎበታል ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ ለትግራይ ክልል የሚቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አሸባሪው ወያኔ ለራሱ በመጠቀም ለሕዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።
ለትግራይ ክልል የተላከ ምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች ቁሳቁስን በመዝረፍ ጭምር የእናቶች፣ የሕፃናትና አጠቃላይ የሕዝቡ ጠላት መኾኑን በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
ለአብነትም ከሦስት ዓመት በፊት ከፌዴራል መንግሥት የተላኩ 250 አንቡላሶችን ለወታደር ማመላለሻነት እንዲውሉ ማድረጉን አንስተዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በ27 ዓመታት በሀገሪቱ ለፈፀመው ግፍ በሕግ ተጠያቂ እንዳይኾን እኔ ከሞትኩ በሚል በጦርነት እድሜውን ለማራዘም እየጣረ መኾኑን ዶክተር አረጋዊ ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ አባል አቶ ባርያገብር አባይ፤ አሸባሪው ወያኔ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ክሕደት ሲፈጽም የመጣ አሁንም በተመሳሳይ ተግባሩ የቀጠለ የሕዝብ ጠላት መኾኑን ገልጸዋል።
የትግራይን ሕዝብ ሲደግፍና ሲጠብቅ የነበረውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸምን ጨምሮ በጦርነት ተጠምዶ ያለ የሰላም ጸር መኾኑንም ጠቅሰዋል። መረጃው የኢዜአ ነው።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
