“ባለብዙው መክሊት ሀዲስ ዓለማየሁ!”

227
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በየትኛው ዘርፍ እንደማታነሳቸው ማሰብ ይከብዳል፡፡ ምዕራባዊያን ግን ወደው ሳይሆን ተገድደው ይህንን ሙሉ ሰው በጸጸት ያስቡታል፤ በሚገባ ነግሯቸው አልገባቸውም መክሯቸው አልተረዱትም፡፡
ዓለም ዛሬ ላይ በሚጨነቅበት የኒውክለር ማብላላት ጅማሮን ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት ሀገራቸው ኢትዮጵያን ወክለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፊት ቆመው፤ ተው ይኽ ነገር አይሆንም ብለው ተናግረው ነበር፡፡
በድርሰቱ የጥበቡ ዓለም ውስጥ የተባ ብዕረኛ ናቸው፡፡ ሀገር ስትወረር እና ድንበር ሲደፈር ቆራጥ አርበኛ ነበሩ፡፡ ሀገራቸውን በቀሪው ዓለም ዘንድ በማስተዋወቅ አንቱታን ያተረፉ ጉምቱ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል፡፡ መራሄ መንግስትነታቸው ከግል ክብር እና ሆድ አደርነት የራቀ ስለነበር አሁንም ድረስ በብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ አይረሴ ሰው አድርጓቸዋል፡፡
ሴናተር፣ የትምሕርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዳይሬክተር፣ ቆንሱል፣ በተመድ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ወኪል፣ የተመድ ባለሙያ፣ አምባሳደር እና የልማት ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን ከአዲስ አበባ እስከ አትላንቲክ፣ ከኒው ጀርሲ እስከ ኒው ዮርክ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ሎንዶን በቅንነት፣ በታማኝነት እና በታታሪነት አገልግለዋል፡፡ እውቁ የድርሰት ሰው ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ፡፡
ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ የሀገሬው ሰው አብዝቶ የሚያውቃቸው በተባ ብዕረኛነታቸው ነው፡፡ ፊደል የቆጠረ እና አስኮላ የተማረ ኢትዮጵያዊ ሆኖ “ፍቅር እስከ መቃብርን” ያላነበበ አይኖርምና ሁሉም ያውቃቸዋል፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር፣ ወንጀለኛው ዳኛ እና የልም እዣት መጽሃፍት ባለቤት የሆኑት ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ የአበሻ እና የወደኋላ ጋብቻ፣ ተረት ተረት የመሰረት እና ትዝታ የተሰኙ ተውኔቶችንም ደርሰዋል፡፡
ጥቅምት 07/1902 ዓ.ም ይህችን ዓለም የተቀላቀሉት ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ፤ የተወለዱት በዘመኑ አጠራር በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረ ማርቆስ አውራጃ በጎዛመን ወረዳ እንዶዳም ኪዳነ ምህረት ቀበሌ ውስጥ ነበር፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ደስታ ዓለሙ ሲባሉ አባታቸው የኔታ ዓለማየሁ ሰለሞን የታወቁ ሊቅ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
ልክ የዛሬ 113 ዓመት የተወለዱት ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ፤ በብዙ መመዘኛዎች የኢትዮጵያዊነት ሚዛን ነበሩ ይባልላቸዋል፡፡ በደብረ ወርቅ እና ዲማ መንፈሳዊ ትምሕርት የቀሰሙት ሀዲስ፤ ወደ አዲስ አበባ አቅንተውም ከስዊድን ሚሽነሪ እስከ ተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
በአምስቱ ዓመታት የአርበኝነት ዘመን ለሀገራቸው ክብር እና ለሕዝባቸው ፍቅር ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱት ጀግና በምርኮ ተግዘው በፖንዞ እና በሊፓሪ ደሴቶች በእስር ላይ ቆይተዋል፡፡ ከእስር ከተመለሱ በኋላም ሀገራቸውን በተለያዩ የኃላፊነት ዘርፎች በቅንነት አገልግለዋል፡፡
“ባለብዙው መክሊት ሀዲስ ዓለማየሁ” ለሀገራቸው በተለያዩ ዘርፎች ላበረከቱት አስተዋፅኦ በሕይዎት እያሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ አበርክቶላቸዋል፡፡ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉትም ህዳር 26/1996 ዓ.ም ነበር፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መልካም ልደት እና የሰላም እረፍት ይመኝላቸዋል!
በታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሰንደቅ ዓላማችን የነጻነታችን ቀንዲል የሉዓላዊነታችንም ማኅተም ናት!
Next articleኢትዮጵያ በአፍሪካ-ሕንድ የመከላከያ ኃይል ውይይት ላይ እየተሳተፈች ነው።