
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰንደቅ ዓላማ አንድ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለበትን የጽናት ደረጃ ማሳያ ነው። ለሰንደቅ ዓላማችን ያለን ክብር ሕዝብ ለሀገረ ያለውን ክብርና የሚከፍለው ዋጋ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያውያን በተለያየ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ብናልፍ፣ መሪዎች ቢቀያየሩ፣ ትውልድ ቢሄድ ቢመጣ ለዘመናት ከማንለውጣቸው የሀገረ መንግሥቱ አንድነትና ጸንቶ መኖር ማሳያ ከሆኑን ቋሚ እሳቤዎች ውስጥ አንዱ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ነው።
ከለውጡ በፊት በነበሩት ሁለት አስርት ዓመታትና ከዚያ በላይ ከብሔራዊ ማንነታችን ይልቅ ለቡድን ማንነቶች የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ብቻ ሳይሆን የቡድን ማንነት ማዋለጃ መሰረቶቹ ሀገረ መንግሥቱን ሊያፈርስ በሚችል የጥላቻ አምዶች ላይ የቆመ ሆኖ በመቆየቱ ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች። አሁንም ከዚህ ችግር የተቀዳውን ፈተና ለማሸነፍ እየታገልን እንገኛለን።
ሰንደቅ ዓላማችን የሀገር ምልክትና ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የከፈሉት መስዋእትነት የሚዘከርበት ልዩ ምልክት መሆኑን መዘንጋትና ማዋረድ ሀገርን ለመክዳትና
ብሎም ለማፍረስ ለሚጋብዙ ትልልቅ ወንጀሎች መግቢያ በር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
የአንድ ሀገር ሕዝብ እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ከሚያደርጉት የጋራ መግባባት ማሳያዎች አንዷ ሰንደቅ ዓላማችን መሆኗን መዘንጋት የለብንም።
ሕዝብ የሚግባባበት አንድ የመንግሥትነት ጥላ፣ በሕዝብ ተሳትፎ (መስዋእትነት) የተረጋገጠ አንድ ሉዓላዊት ሀገር፣ ክፉውን አርመን በጎውን የምናሳድግበት አንድ የጋራ ታሪክ የሚኖረው መጀመሪያ በአንዲት ሰንደቅ ዓላማ ሥር ቁሞ ኢትዮጵያዊ መባል ሲቻል ነው።
ስለሆነም የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሰንደቃችን የብሔራዊ መግባቢያ አንዱ መሣሪያችን እንደመሆኑ በአንዲት ሰንደቅ ዓላማ ሥር ቁመን፤ በአንድነት ፈተናዎችን ተሻግረንና ድህነትን ድል ነስተን፤ ብልጽግናችን እውን ለማድረግ የኅብረታችንን ውል የምናጠብቅበት እለት መታሰቢያ ነው።
የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር እለቱን በማሰብ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን የዚህ ትውልድ አባል እንደመሆናችን ሰንደቃችን የነፃነታችን ቀንዲል፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም መሆኗን በውል ተገንዝበንና ከልብ ተቀብለን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን በፅናት የምንቆምበት እንዲሁም በዘላቂነት በሰንደቃችን ላይ የማይደራደር ትውልድ ሆኖ መገኘት ይጠበቅብናል።
በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ አሸናፊና ውጤታማ በመሆን ሁሌም ለሰንደቅ ዓላማችን ታማኝ ዘብ ሆኖ በተግባር መገኘትም ይገባናል።
መረጃው የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!