
አዲስ አበባ: ጥቅምት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር ሀጅ አወል አርባ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ታሪክ ፣ የጋራ ሕግና ባሕል ፣የጋራ መንፈስና ስብዕና ፤ከሁሉም በላይ በጋራ ተስፋ የተሳሰረ ቤተሰብ እንጂ በልዩነት ያሉ ሕዝቦች ውጤት አይደለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት በሕዝብ የእለት ተእለት ህይወት ሰፊና ጥልቅ መሰረት በመያዙ ምክንያት አንድ ችግር ሲገጥም አንድ በመኾን ብዙ ሆኖ መመለስ ነው ፤ይህንን እሴት ደግሞ በተግባር አይተንዋል ይላሉ ሀጅ አወል አርባ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ማለት የሕይወት ምንጭነት፣ የስብእና መገኛ ሥፍራ ማለት ነው የሚሉት ርእሰ መስተዳድሩ ኢትዮጵያዊነት ማለት የሥልጣኔ መጀመሪያ ፣የሰው ዘር አርዓያ፣ የሥነ ምግባር ልዕልና ማለት ነው ነው ያሉ፡፡
ሀጅ አወል አርባ ኢትዮጵያዊነት ማለት የሀገርነት ፣የጀግንነት እና የፍትሐዊነት ተምሳሌት ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ እናም በዚህ ማንነት ከመኩራት ውጭ አማራጭ የለም የሚሉት ርእሰ መስተዳድሩ አብሮ ለመሥራትም ብዙ ሀብት ስለመኖሩ ገልጸዋል፡፡
ሀጅ አወል አርባ ኢትዮጵያን ሊያፈራርሱ የሚሹ ብዙዎች ቢነሱም የቁርጥ ቀን ልጆቿ ሃሳብን በሃሳብ፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ኀይልን በመግባባት አለፍ ሲልም እንዳመጣጡ እያስተናገዱ ሀገርን ከባሕሏ፣ ከማንነቷ እና ከክብሯ ጋር በማስቀጠል ለእኛ አድርሰዋል አሁን ሀገርን የማስቀጠል ተራው የእኛ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አብነት እስከዚያ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!