
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም እንደሚከበር ተገልጿል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ ስለ ሰንደቅዓላማ ቀን አከባበር በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
“ሰንደቅ ዓላማችን የብዝኃነት መገለጫ የሉዓላዊነት ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ሐሳብ የፊታችን ሰኞ እንደሚከበር ምክትል አፈ ጉባዔው በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
መሪ ሐሳቡ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር በሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን ክንድ መክተን እንሻገራለን የሚል መልእክት እንዳለውም አቶ አማረ አብራርተዋል። ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነትና የመቻቻል ዋስትና መኾኑ በመሪ ሐሳቡ ሌላኛው የሚካተት ጉዳይ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት።
“ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነትና የነጻነት ምልክት ነው” ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔው ዕለቱ በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበርም አስረድተዋል።
አቶ አማረ እንዳሉት 15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአማራ ክልል ለወገን ጦር ደም በመለገስ፣ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች ይከበራል።
በበዓሉ ሀገር ለማፍረስ የጣሩ አካላት እንዳልተሳካላቸው የምናሳይበት ቀን ይኾናል ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔው የወገን ጦር የሚዋደቁበትና የሚታገሉበት ምክንያት ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገር ክብር ስለኾነ በክልሉ ይኽን በሚያመላክት ዝግጅት በድምቀት ይከበራል ብለዋል።
በዓሉ በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት የተለያዩ ግብረኀይሎች ማቋቋሙን የተናገሩት አቶ አማረ በባሕር ዳር ከተማ በሚሊኒየም አደባባይ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል። በዕለቱ ነዋሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚሳተፉበትም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!